ሄርማስ፡ታትያን፡ቴዎፍሎስ እንዲሁም ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ በነበሩበት ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ ተብሎ በሚታወቀው ዘመን የነበረ ክርስቲያንና ፈላስፋ ነው አቴናጎራስ፡፡ ከዚህም ሌላ አርጌንስና ጠርጡለስ በነበሩበት የሁለተኛ መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳ ፍቱን ብዕርና የዳበረ አዕምሮ የነበረው ሰው ነው፡፡
ስለ አቴናጎራስ የሚያወሱ ሁለት የጥንት ቤተክርስቲያን መዛግብት ብቻ
ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም፤
- ኤጲፋንዮስና ፎጢኖስ መዝግበው ባስቀመጡት ስለ ሰውነት ትንሣኤ በሚናገርው በሜቶዲየስ በተዘጋጀው ጽሑፍ ላይ
- በፓምፊሊያ ባንጸባረቀው ፊሊጶስ ዘሲዴ በጻፈው ላይ ናቸው፡፡
አቴናጎራስ አስቀድሞ የአቴና ፈላስፋ ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመንቀፍ
ሲያነብባቸው በትምህርታቸው ተስቦ ክርስቲያን እንደሆነ ፊሊጶስ ዘሲዴ ጽፏል፡፡
አቴናጎራስ ብዙ እንደጻፈ ቢታመንም አሁን ድረስ ተጠብቀው ያሉ ስራዎቹ
ግን ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ስለ ክርስቲያኖች የጻፈው የጥብቅና ጽሑፍና ስለሙታን ትንሣኤ የጻፈው ናቸው፡፡ አቴናጎራስ ባለ ብሩህ አዕምሮ፣የዳበረ ልምድ ያለው ጸሐፊ፣ ጥልቅ ነገርን
በሚገባ(ለመረዳት በሚያስችል) መልኩ መጻፍ የሚችል፣ ታዋቂ ከሆኑ ከጥንት የቤተክርስቲያን ጠበቆች አንዱ እንደሆነ በእርግጠኝነት
የሚመሰከርለት ነው፡፡
ስለ ክርስቲያኖች
የጻፈው ጥብቅናው በሰላሳ ሰባት ምዕራፎች፣ ስለሙታን ትንሣኤ የጻፈው ደግሞ በሃያ አምስት ምዕራፎች ተከፋፍለው ይገኛሉ፡፡
በጥብቅና ሥራዎቹ ውስጥ ትኩረት የሰጣቸው ጉዳዮች፡ በክርስቲያኖች ላይ ስለሚነሱ ክሶች የአግባብነት ጉድለቶች፣ ስለሚሰጣቸው
ኢ-ፍትሐዊ ፍርድ፣ ስለሚፈጸሙባቸው አድሎዎች፣ ስለ ክርስቲያኖች ሞራላዊ ልዕልና፣ በክርስቲያኖችና በከሳሾቻቸው መካከል ስላለው ሰፊ
የሞራል ልዩነት፣ በአንድ አምላክ ማመን፣ በአንድ አምላክ ስለ ማመን
የባለ ቅኔዎችና የፈላስፎች ዕይታዎች፣ ሐሰት ስለሆኑ የጣኦቶች አምልኮዎች የሚሉ ይገኙበታል፡፡
የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ በጻፈው ጽሑፉ ውስጥ ትንሣኤ የሚቻል እንደሆነ፣ ልዩ ልዩ የትንሣኤ ምሳሌዎች፣ በትንሣኤ ጊዜ
ስለሚኖረን ሰውነት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ከትንሣኤ ሙታን ጽሑፎቹ ውስጥ የተወሰኑት እንደሚከተለው
ተተርጉመው ቀርበዋል፡፡
No comments:
Post a Comment