ለዛሬ ንነጽር ከተሰኘው ካልታተመው ጽሑፌ ትንሽ ላጋራችሁ
ወደድሁ፡፡ ይህም በአመክንዮ፣ ፍልስፍና፣ እውቀት፣ እምነትና እውነት የሚያተኩር ሲሆን የተወሰነውን ይዘት በሁለት ክፍል አቀርባለሁ፡፡
መልካም ንባብ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎታቸው ሂደት የሚገጥማቸውን ፈተና ለማለፍ እንደ እባብ ልባም እንደ
ርግብም የዋህ እንዲሆኑ ሐዋርያትን መክሮአቸዋል። ሐዋርያት እንዴት፣ እንደማንና ምን ያህል የዋህ መሆን እንዳለባቸው ለርግብ ያላትን የዋህነት በመግለጽ
አስረዳቸው። ርግብን የዋህ የሚያስብሉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በወንጌሉ አንድምታ ከተጠቀሱት አንዱ ርግብ በቀል የሌላት መሆኑ
ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ርግብ የዋህ ሁሉ ሲል ቂም በቀል አትያዙ፣ ኃዳግያነ በቀል ሁኑ ማለት ነው፡፡ ማቴ.10፣16
“እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡”
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በትንቢተ ኢሳይያስ ም.53 ቁ.7 ላይ የተጻፈውን ሲያነብብ ነበር ፊልጶስ ተርጉሞ እንዲያስረዳው በመንፈስ
ቅዱስ የተላከው፡፡ የሐዋ.8፣32
ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኋላ ዘመን የሚቀበለውን መከራ፣ የሚቀበልበትንም የትዕግስት
መጠን ለማሳየት የሞከረ ነው፡፡ የጌታችን ትዕግስት ለመታረድ የሚነዳ በግ በሚያሳየው ትዕግስት ተመስሏል፡፡ በግ በአራጁ ፊት በየዋህነት
ያለ ማንገራገር እንደሚቀርብ ሁሉ ጌታችንም ሲዘብቱበትና ሲገርፉት፣ ሲሰቅሉትና መከራ ሲያጸኑበት እስከሞት ድረስ ታግሷልና፡፡
ርግብ ያላት የዋህነት ሐዋርያት እንዲኖራቸው ሲመከሩ በግ ያለው ትዕግስት ደግሞ የክርስቶስ ትዕግስት
ማስረጃ(የሚያስረዳ) ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይህም ማለት ሐዋርያት ርግብን በሁሉም ነገሯ ሊመስሏት በግም በሁሉም ነገሩ የክርስቶስ ማሳያ
ሊሆን አይጠበቅም፡፡ ስለዚህም ከላይ
በተጠቀሱት ውስጥ ምሳሌዎች አማናዊዎቹን(እውነተኛ የተጠቀሱ አካላትን) በምሉእነት ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ይወክላሉ፡፡
አመክንዮም/ሪዝኒንግ እንዲሁ ነው። አመክንዮ ከተሳካለት እውነትን በምልአት
ይገልፃል። ካልሆነ ግን እውነትን በተወሰነ መልኩ ከመግለፅ የዘለለ አቅም አይኖረውም። ሲጀመር አመክንዮ ያስፈለገው እንደመሰላል
መወጣጫ ሆኖ፣ እንደመስታወት ማቅረቢያ ሆኖ እውነትን ለመረዳት እንዲያስችል ነው።
አመክንዮ ነገሮች እንዴት እውነት እንደሆኑ ወይ እንዴት ሐሰት እንደሆኑ ለሕሊናችን በቀረበ መልኩ ለማስረዳት ከሚያገለግል
በቀር የእውነት መኖር ማረጋገጫ የመሆን አቅም ላይኖረው ይችላል፡፡ አመክንዮ ስለ እውነት/እውነትን ለማብራራት ይኖራል አንጂ እውነት
ስለ አመክንዮ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ሁሉንም እውነት በአመክንዮ ልንደርስበት አንችልም፤ አመክንዮ የማይደርስበት እውነት አለና፡፡
እውነት አስቀድሞ አለ፤ አመክንዮ የእውነት መገለጫ ሆኖ ስለ እውነት ይኖራል። የአመክንዮ መታጣት (አብራርቶ ማስረዳት አለመቻል) የእውነትን መታጣት ወይ አለመኖር አያስረግጥም። አመክንዮ እውነትን መግለፅ ከቻለ እሰየው፤
ካልቻለም አመክንዮ የማይበልጠው እውነት እንዳለ እናስተውል። ስለዚህም እውነት ከአመክንዮ ከመብለጡ የተነሳ እምነት ከእውቀት በላይ
እንደበለጠ ይኖራል። ይህም አገላለፅ በራሱ አመክንዮ ነው- አመክንዮ እውነትን ለመግለጽ ሲጣጣር።
ፍልስፍናን ከዚህ አንጻር ስንመለከተው ከእውነቱ ጋር ከሚያገናኘን ገላጭ/ ፈላስፋ የመግለጽ አቅም ጋር በእጅጉ የተገናኘ
እንጂ እውነትን ነጻ የሚያወጣና በራሱ እንዲገለጽ እድል የማይሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም መንገድ አንድን ሐሰት የሆነን ነገር/አስተሳሰብ
ጥሩ አድርጎ ማስረዳት በሚችል ፈላስፋ አማካይነት እውነት ነው ብለን እንድንቀበል ልንገደድ እንችላለን፤ እንዲሁም አንድን እውነት
የሆነን ነገር/አስተሳሰብ ጥሩ አድርጎ ማብራራት በሚችል ፈላስፋ አማካይነት ሐሰት አድርገን እንድንቀበል ተጽእኖ ሊያሳድርብን ይችላል፡፡
ለዚህም ይሆናል በፍልስፍና ውስጥ ራሱ የአመክንዮ መርሆዎች አግባብነትን የሚያጠና ሎጂክ የሚባል ክፍል ሊኖር የቻለው፡፡
ይህም በራሱ እየተጠና የሚሄድ በየጊዜው የሚሞገት እንጂ ያለቀለት ይህ ነው ሊባል የሚችል ነገር አይደለም፡፡ እንዲያም ሁኖ ሁሉም
በየመንገዱ “እውነት የሆነው ይህ ነው” በሚል አልያም “ይህ እውነት አይደለም” በሚል ፍልስፍናን መሰረት አድርጎ ይከራከራል፡፡
ነገር ግን ፍልስፍና ሁሉንም ነገር በብቃት የመመለስ አቅሙ በአስረጂዎች እጅ ያለ በመሆኑ እውነትን ወደ ራሱ ደረጃ ዝቅ
አድርጎ በማሰብ በመሳሪያው ፈልጎ የማይደርስbት ከሆነና ምናልባትም “እውነት የሚባል ነገር የለም” እስከማለት የሚደርስ ከሆነ ሌላ
ርግጥ የሆነና ወደ እውነት የሚያደርስ መንገድ ይኖር ይሆንን?
እዚህ ላይም ቢሆን ከላይ አመክንዮን እምብዛም መሻገር የማይችለው ብለህ የገለፅከውን ፍልስፍና እየተፈላሰፍክ ነው ሌላ
መንገድ መሻትህ በራሱ ፍልስፍና ነው ያሰኝ
ይሆናል፡፡ አዎን ፍልስፍና ተብሎ ይሰየም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከላይ ከገለጽኩትና ሁሉንም ነገር
በአመክንዮ ቀንበር ስር አድርጎ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ቢኖርም እንኳ “በሰው ልጅ አቅም መርምሬ እደርስበታለሁ” ከሚለው አስተሳሰብ
የተለየ አካሄድ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment