እውቀት፣
እምነት፣ እውነት
በፍልስፍናው ዓለም እነዚህን ሦስት ነገሮችን
የተመለከቱ ልዩ ልዩ አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ እውቀትን የነገሮች ሁሉ የበላይ አድርገው የሚያስቡ ወገኖች አሉ፤ ከዚህ የተነሳም
የክርስትናን እምነት በእውቀት ብቻ ሊመሩ ሲሞክሩ ተሰነካክለው ወድቀዋል፡፡
በሌላው ጥግ ደግሞ እውቀትን የእምነት ጠላት
አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አዋቂዎች የማያምኑ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ እምነትን የእውቀት ጠላት አድርገው የሚያስቡት ደግሞ አማኞች አላዊቂ
እንደሆኑ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
እውነት በእውቀትና እምነት ትገለጻለች
የካምብሪጅ የፍልስፍና መዝገበ ቃላት እውቀት
የተረጋገጠ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ በማለት አውቀት፣ እምነትንና አውነትን ያስተሳስራቸዋል፡፡ አምነት ማረጋገጫው ምንድነው? እንዴትስ
ይረጋገጣል? በሚለው ግን በክርስትናው እምነትና በዓለማዊው ፍልስፍና መካከል ልዩነት አለ፡፡
እምነትና እውቀት ስለ እውነት የሚመሰክሩና ወደ
እውነት የሚያደርሱን ናቸው፡፡ ከሰዎች ልጆች የመረዳት አቅም በላይ፣ ከስሜት ሕዋት የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነውን ይህን እውነት በእምነትና እምነትን መሰረት ባደረገ እውቀት እንረዳዋለን፡፡
እውነት በእምነትና በእውቀት ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ
በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት ውስጥ እግዚአብሔር አብ(አባት) ከዓለም መፈጠር፣ ከዘመን መቆጠር በፊት እግዚአብሔር ወልድን(ልጅ) ያለ
እናት ወልዶታል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ልደት ይባላል፡፡ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድን ስለወለደው ግን አብ ወልድን በዘመን አይቀድመውም
ይህ ከዘመናት መፈጠር በፊት ነውና፡፡
ይህንን ልደት በሥጋዊ ዐይን ማን አየው; ብንል
ግን ማንም አላየውም ቢያንስ ከፍጥረታት መፈጠር በፊት ስለሆነ፤ በእምነት ግን እናውቀዋለን እምነት ይህንን የመረዳት አቅም ስለሚሰጠን፡፡
የወልድ ከአብ መወለድ እምነት ነው፤ ወልድ ከአብ ተወልዷል የሚለው በራሱ እውቀት ነው፤ ራሱ የወልድ ከአብ መወለድ ደግሞ እውነት
ነው፡፡ ስለዚህም የወልድ ከአብ የመወለድ እውነት በእምነት እናውቀዋለን፡፡ እውነትም በእምነትና
እውቀት ይገለጻል፡፡
እውነት ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልገውም
የእውነት ማረጋገጫ ራሱ እውነት ነው፡፡ በመጽሐፍ
ቅዱስ እንደምንረዳው እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ ማረጋገጫ የምንለው ከሚረጋገጠው ነገር በላይ ነውና ከእግዚአብሔር በታች የሆኑ ነገሮችን በእግዚአብሔር እናረጋግጣቸዋለን፡፡ ከእግዚአብሔር
በላይ ማረጋገጫ ማግኘት ስለማይቻል ለእውነት ሌላ ማረጋገጫ የላትም፡፡
እውነት በገዛ ራሷ የቆመች ሌላ ማረጋገጫ የማትሻ ናት፡፡ በሌላ ማረጋገጫ ተመዝና የምታልፍና የምትወድቅ ሳትሆን እውነት እውነትነቷን
መጠበቅና ማረጋገጥ የምትችል የገዛ ራሷ ባለስልጣን ናት፡፡ ስለዚህም ሌሎችን በእውነት እናረጋግጣለን እንጂ እውነትን በሌላ ነገር
አናረጋግጥም፡፡
በሒሳብ ትምህርት ውስጥ እንደ እውነት የሚቆጠሩና
ሌላውን ለማረጋገጥ የምንጠቀምባቸው አሉ፡፡ እነዚህም አግዚዮምስ እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ በግሪክ ቋንቋ አግዚዮም ማለት በራሱ የተረጋገጠ
የሚል ነው፡፡ እውነትም እንዲሁ በራሷ የምትረጋገጥ እንጂ በሌላ አትረጋገጥም፡፡
ዮስጢኖስ ሰማዕት ስለ ትንሳኤ በጻፈው ጽሑፍ
ከእውነት በላይ ኃያል የሆነና ከእውነት በላይ ሊታመን የሚገባው ነገር
ስለሌለ እውነትን በሌላ አናረጋግጠውም በራሱ የተረጋገጠ ነው እንጂ፡፡ ነገር ግን የእውነትን ማረጋገጫ የሚፈልግ ሰው ነገሮች ለስሜታችን
እንደሚገለጡት ሆነው ለምን ተገለጡ የሚልን ሰው ይመስላል፡፡ በአመክንዮ የሚመጡ ነገሮች መመዘኛ ስሜት ነውና ለስሜት ራሱ ግን ከእርሱ
የሚበልጥ ሌላ መመዘኛ የለውም፡፡ ብሏል፡፡
የእምነት መገለጫ
በራስ አመለካከት አለመደገፍ
በአመክንዮ የምንረዳቸው ነገሮች ቢኖሩም በአመክንዮ
የማንረዳቸው ግን ደግሞ ያሉና እውነት የሆኑ ነገሮችም አሉ፡፡ ከስሜት ሕዋሶቻችን የመረዳት አቅም በላይ ከአመክንዮ የመግለጽ አቅም
በላይ የሆኑ ናቸውና፡፡ እምነት አመክንዮ የማይደርስባቸውን ነገሮች የምትመረምርና የምታስረዳ መሳሪያ ስለሆነች እውነትን በራሳችን
አስተሳሰብ ብቻ ስንገድባት በአመክንዮ ልክ እናስቀራትና ወደ እውነት ሳንደርስ እንቀራለን፡፡
ስለዚህ እምነት የራስን አመለካከትንና መረዳትን
ብቻ ትክክል ነው ከማለት የተለየ የራቀ ነገርን ትፈልጋለች፡፡ ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ እምነት ንቁና ነጻ የሆነችን ነፍስ ትፈልጋለች፣ ከሰው ልጆች የአመክንዮ ጉድለት በላይም ከፍ ከፍ ያለችን ነፍስ
ትፈልጋለች ይላል፡፡ ዕብ.11 ትርጓሜ አመክንዮ የራሱ ጉድለት ያለበት ከሆነ እና እምነት ደግሞ ከአመክንዮ አቅም
በላይ የሆኑ ነገሮችን የምንመረምርበት መሳሪያ ከሆነ ከአመክንዮ እስራት መፈታትና ነጻ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በዕብ 2፣4 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ሲባል ይሞኛል ማለት ሳይሆን ነፍሳችን ከአመክንዮ
አስተሳሰብ በላይ ካልሆነች እውነትን መረዳት አትችልም ማለት ነው፡፡
ፍላጎትንና
ችሎታን ትጠይቃለች
ችሎታን የሚጠይቅ ነገር ታላቅ ነገር እንደሆነ ግልጽ ነውና፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ የእምነት ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ብዙዎች እምነት ሞኝነት፣ ቸልተኝነት እንዲሁ ለሁሉም የሚሆን ይመስላቸዋል፡፡
እምነት በአንጻሩ ትልቅነትን፣ አስተዋይነትን ፍላጎትንና ችሎታን ይጠይቃል፡፡ ችሎታና ፍላጎት የሌለው ሰው አማኝ ሊሆን አይችልም፡፡
እምነት ሞኝነት ሳይሆን ከአመክንዮ ከፍ ያለ ችሎታን የሚጠይቅ ነው፡፡
በዮሐ.6፣60 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው
ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ
እኖራለሁ። ዮሐ.6፣54-56 ብሎ ስለ ቅዱስ ቁርባን ባስተማረ ጊዜ ከሚከተሉት ብዙዎቹ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው ማን ሊሰማው ይችላል
ብለው ወደ ኋላ ተመለሱ፡፡
በእምነት መስማት ያለብንን በአመክንዮ ብቻ ከሰማነው ከመደመጥ አቅም በላይ ይሆንና የሚያስጨንቅ ይሆናል፤ በእምነት ማየት
ያለብንን በዐይናችን ብቻ ካየነው ከዐይናችን የማየት አቅም በላይ ይሆንና የተሳሳተ ነገር አድርገን እንወስደዋለን ከእውነትም እንርቃለን፡፡
ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ማን ሊሰማው ይችላል ብለው ብዙዎቹ
ወደ ኋላ የተመለሱት ትምህርቱ የተሳሳተ ስለሆነ አይደለም አስተማሪው እውነት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ነገር ግን ተማሪዎቹ
መረዳታቸው ዝቅተኛ ስለነበረ በራሳቸው አመክንዮ ብቻ ስለገመገሙት ችሎታቸው ደካማ ስለነበረ ወደዚህ ከፍ ያለና በእምነት ወደሚደረስበት
ነገር ለመድረስ ሲቸገሩ እንመለከታለን፡፡
ስለዚህ እምነት አእምሮአቸውና አስተሳሰባቸው ትንሽ የሆኑ፣
የሥራ ፈቶችና የደካሞች ሳይሆን አእምሮአቸውን ከፍ ከፍ ያደረጉ፣ ልባቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ፣ የአስተዋዮች ነው፡፡ ሰው የሚያምነው
ሥራ ፈትና ተራ ነገር ስለሆነበት ሳይሆን አእምሮውን ከፍ ስላደረገ፣ አስተዋይ፣ ታታሪ ሠራተኛ ስለሆነ ነው፡፡
በአንጻሩ አስራ ሁለቱን ሐዋርያትን እናንተ ደግሞ ልትሔዱ
ትወዳላችሁን ባላቸው ጊዜ በስምዖን ጴጥሮስ በኩል ጌታ ሆይ፥
ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል
አውቀናልም፡፡ ብለዋል፡፡
ይህ የሚያሳየው ወደ ኋላቸው ከተመለሱት ይልቅ ሐዋርያት የተሻለ ዐይን፣ የተሻለ ጆሮ፣ የተሻለ ችሎታ እንደነበራቸው ነው፡፡
እነዚያ የሚያስጨንቅ ንግግር ማን ሊሰማው ይችላል ብለው ተስፋ
ቆርጠው ሲያስቆርጡ እነዚህ ግን ወደ ማን እንሄዳለን አንተ የዘላለም
ሕይወት ቃል አለህ በማለት እውነትን ተረድተውታልና፡፡
የጌታችን ንግግር ለእነዚያ የሚያስጨንቅና ሊሰማ የማይችል ሲሆንባቸው ለእነዚህ የዘላለም ሕይወት ቃልና የሚገባ(ባ-ላልቶ
ይነበብ) ሆኖላቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ሃይማኖት የታታሪዎች እንጂ የሰነፎች አይደለም፡፡
No comments:
Post a Comment