የሰው ልጅ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ ለፍለጋ ከማነሳሳት እና
እውነትን ከመግለጥ አንጻር ፋይዳው ከፍ ከሚሉት አንዱ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ በርግጥ ማን ነህ? ማን ነሽ? የሚሉ ጥያቄዎች ለሰው
ልጅ ሲቀርቡ በቀበሌ መታወቂያቸው ላይ የሰፈረውን መረጃ መጥቀሱ መልስ ሊሆን ይችላል፤ እዚያ ላይ ሙሉ ስም፣ ጾታ፣ ዜግነት፣ የትውልድ
ቦታ፣ ዕድሜ፣ ሥራ፣ የትዳር ሁኔታ፣ ቀበሌ፣ የመኖሪያ ቤት ቁጥር፣ የስልክ አድራሻ… ተጠቅሰዋልና፡፡ ሰዎችም የሰዎችን መታወቂያ በማየት ስለ እነዚያ ሰዎች ከላይ
የተጠቀሱትን ግንዛቤዎችን ያገኛሉ፤ መታወቂያው ሐሰተኛ ካልሆነ፡፡
ይህ ሁሉ መረጃ ግን የማንነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የቻለው
አስቀድሞ አንድ ትልቅ የማንነት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ነው፡፡ ይኸውም “ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ “ሰው ነው” የሚል መልስ ስላገኘ፡፡
እናም መታወቂያው ሰው ለመሆናችን ምክንያት ባይሆንም ሰው መሆናችንን ይመሰክራል፡፡ የአንድን አካል ማንነት በአግባቡ አለማወቅም
ለስህተት ይዳርጋል፤ በተለይ የዚያ አካል ማንነት በሌሎቹ ላይ የሚኖረው ድርሻ ትርጉሙ ከፍ ያለ ሲሆን፡፡
አንድ ለማንነት እውቅና የሚሰጥ አካል ለአንድ ሰው ፍጥረቱን
ዝቅ አድርጎ ዝንጀሮ የሚል ማንነት ቢሰጠው ወይም አኗኗሩን
ከፍ አድርጎ መልአክ የሚል ማንነት ቢሰጠው ይህ የተሰጠው አዲስ
ማንነት ሰውዬዉን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላሉ ፍጥረታት በሙሉ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ሰውን ዝንጀሮ የሚል ማንነት ሲሰጡት በአኗኗሩ እንደ ዝንጀሮ በዱር ወይ በፓርክ ውስጥ፣ ጋብቻው ከዝንጀሮ ጋር እንዲሆን
ይጠበቃል፣ ሰው ስለመሆኑ እውቅና አልሰጠውምና በሥጋ ያሉት ዘመዶቹ እንዲለዩት … ሲሆን መልአክ የሚል ማንነት ሲሰጡት ደግሞ የቀበሌ ስኳርና ዘይት ብቻ ሳይሆን ከነአካቴው ምግብ አያስፈልገውምና አይብላ፣
መጓጓዣ ኣያስፈልገውም፣… አይሳሳትም፣ …ተብሎ ይቆጠራል፡፡
ስለዚህም የማንነት ጥያቄ ታላቅ የሚሆነው በአንድ በኩል ትክክለኛ
ምላሽ ሲያገኝ እውነትን የምናውቅበት መንገድ ስለሆነ ሲሆን በሌላ በኩል ደግም ትክክለኛ ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር ከእውነት ፈጽሞ የምንርቅበት
እና የምንጠፋበት ስለሆነ ነው፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ እና ምላሽ
ሲሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ ከምላሽ ሰጪው አካል ወይ ከጠያቂው አካል እውነተኛነት፣ ፍላጎት፣ እውቀትና ዝግጁነት የተነሳም የተለያዩ
ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ጥያቄ ያልቀደማቸው ምስክርነቶችም አሉ፡፡
መነ ትብል
ርእሰከ?
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አይሁድ ስለ ማንነቱ በጠየቁት
ጊዜ የሰጠው ምላሽ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም የሚል ነው፡፡
ዮሐንስ በምድረ በዳ ያደገ፣ በብህትውና የኖረ፣ ሰዎችን በውሀ የንስሐን ጥምቀት ሲያጠምቅ የነበረ በመሆኑ ለብዙዎቹ ክርስቶስ መስሎአቸው
ነበርና ስለ ማንነቱ ከራሱ ለመረዳት ካህናትንና ሌዋውያንን ልከውበት ነበረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም መልስ መስጠት የጀመረው እርሱ ማን
እንደሆነ በመግለጽ ሳይሆን ማን እንዳልሆነ በመግለጽ ነው፡፡ ይህም ስለርሱ ማንነት በብዙዎች ዘንድ ያለው አረዳድ ክርስቶስ ነው የሚል የተሳሳተ ስለነበረ ያልሆነውን አይደለሁም በማለት
መልስ ሰጥቶአል፡፡ ይህም እንደ ትልቅ ተጋድሎ ተቆጥሮለት መሰከረም
አልካደምም እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ ተብሎ ተጽፎለታል፡፡ በርግጥ ታላቅ ምስክርነት ነበረ፡፡ ከዮሐንስ ተግባራትና
አኗኗር አንጻር ክብር ይግባውና እንደ ሐሰተኞቹ ምድራዊ ስም፣ ዝናና ክብር ለማግኘት ሲል ሐሰተኛ ማንነትን ለራሱ ደርቦ እርሱ ክርስቶስ ነኝ ቢል ብዙዎች ይከተሉት ነበር ፡፡ ክርስቶስን የሚመስል(በመንገዱ) እርሱ ይቅርና ክርስቶስን ከቶ የማይመስሉ የዘመናችን
ሆድ እና ስሜት አምላኪ ሐሰተኛ መምህራንም ቲፎዞ ሲያሰባስቡ እናያለንና፡፡ በዚያ ላይ ከርሱ ማረጋገጫን የሚጠብቁ( ክርስቶስ አይደለሁም
እንዲል ሳይሆን ነኝ እንዲል የሚጠብቁ) ብዙ ተከታዮች በነበሩበት ጊዜ፡፡
ነገር ግን የቅዱሳን አንዱ እና ቀዳሚው መገለጫ እውነተኛነት
ስለሆነ ያልሆኑትን እና የማይገባቸውን ማንነት/ክብር አብዝተው ይርቁታል በቁርጠኝነትም አይገባንም ብለው ትህትናን በሚቀድም እውነታ ይመሰክራሉ፡፡ እርሱ ክርስቶስ ካልሆነ ስለ ራሱ ማንነት እንዲናገር
በተጠየቀ ጊዜ በነቢዩ ኢሳይያስ ስለ እርሱ የተጻፈውን በመጥቀስ የጌታን መንገድ አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምጽ እኔ ነኝ
የሚልን ምላሽ ሰጥቶአል፡፡ የክርስቶስን ማንነት ከራሱ ማንነት ጋር ሲያነጻጽርም የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፣ ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ በኋላ የሚመጣ በሚሉ ሐረጎች ገልጾታል፡፡ዮሐ. 1፣19-27
ሰዎችን መስለው
ወርደዋል
ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ባገኙት ጸጋ ትምህርቱን ከተአምራት
ጋር ያስተምሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከበርናባስ ጋር ሆኖ በልስጥራን ለአገልግሎት በተገኘበት ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን በማስተዋል
ይሰማ የነበረና እምነት የነበረው ከእናቱ ማሕጸን ጀምሮ አንካሳ የነበረ ሰው ቅዱስ ጳውሎስ በታላቅ ድምጽ ተነሳ ባለው ጊዜ ቀጥ
ብሎ በመነሳት ተመላልሷል፡፡ ይህን ያዩ ህዝቡም አማልክት ሰዎችን
መስለው ወርደዋል በማለት ለጳውሎስና በርናባስ ሄርሜንና ድያ
የሚሉ የጣኦታትን ስሞችን ሰጧቸው፤ ካህነ ጣኦታትም መስዋእትን ይሰዋላቸው ዘንድ ኮርማዎችን ይዞ መጣ፡፡
ህዝቡ ካዩት ተአምራት በመነሳት ቅዱስ ጳውሎስንና በርናባስን
መጠየቅ ሳያሻቸው ማንነታቸውን አማልክት በማለት ገልጸውታል፡፡
ዝናን፣ ክብርንና ሐሰትን በሚፈልግ በዚህ ዓለም ዘንድ አምላክ መባልና ተከታይ ማግኘት እጅግ የሚፈለግ ቢሆንም በሐዋርያት ዘንድ
ግን የሐሰት ማንነት ሞት በመሆኑ የተጸየፉትና በጩኸትም ሳይቀር አምርረው የተቃወሙት ነበር፡፡ በብዙ ጭንቅም እነርሱን አማልክት በሚል የተሳሳተ ማንነት እንዳያመልኳቸውና እንዳይሰዉላቸው
አድርገዋል፡፡ በሌላም በኩል የእውነተኛውን አምላክ ማንነት አስተምረዋቸዋል፡፡ ሐዋ.14፣ 11-15
ጌታችንን
በተመለከተ የቀረቡ የማንነት ጥያቄዎችና የሰዎች አረዳዶች
ራሱ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር በነበረበት
ጊዜ ስለ ራሱ ማንነት ከአይሁድም ከራሱም ጥያቄ ቀርበዋል፡፡ አይሁድ ስለ ክርስቶስ ማንነት የነበራቸው አረዳድ ትክክል አለመሆኑ
ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ በተሻለ ሁኔታ የተረዱትን እንኳ መረዳታቸውን ሲኮንኑ ነበር፡፡
ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የነበረውን ሰው ጌታችን ባዳነው ጊዜ
አይሁድ እግዚአብሔርን አክብር ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን በማለት ስለ ክርስቶስ ማንነት በጠየቁት ጊዜ ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም ዕውር እንደነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ
ነገር አውቃለሁ ብሏቸዋል፡፡ ይልቁንም መምህራን ነን ባዮቹን ስለ ክርስቶስ ማንነት አለማወቃቸውን እንዲህ ሲል በአድናቆት
ይናገራቸዋል፡፡ ከወዴት እንደሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር
ነው፤ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ፡፡ ዮሐ.9፣1-30
አንተ ማን
ነህ
? ዮሐ.8፣25
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ ማንነት እና ስለ አይሁድ
ማንነት ሲናገር ይህ ያልተዋጠላቸው ፈሪሳውያን መልስን ሳይሹ ጠይቀውታል፤ መልስን ፈልገው ቢሆን ኖሮ በተለያዩ ጊዜያት የነገራቸውን
እና ያደረጋቸውን ያስተውሉ እና ይረዱ ነበርና፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ ማንነት ከመረዳት ይልቅ እርሱ እንዲኖረው
የሚፈልጉትን የፍጡርን እና የኃጢአተኛን ማንነት ይሰጡት ነበር፡፡ እንግዲህ
አንተ ማነህ? ለሚለው ጥያቄአቸውም ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት
ነኝ የሚል ምላሽ ሰጥቶአቸዋል፡፡
ራስህን ማንን
ታደርጋለህ ? ዮሐ.8፣53
እውነት እውነት
እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም፡፡ የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ተከትሎ አይሁድ ነገሩ እውነትነት የሌለው
አድርገው በመቁጠር በስላቅ የጠየቁት ነው “ራስህ ማንን ታደርጋለህ?” የሚለው፡፡ ለዚህም ማሳያ እንዲሆናቸው የሚከተለውን አመክንዮ
ተጠቅመዋል፡፡ የያዙት አመክንዮም በእነርሱ አረዳድ እጅግ ጠንካራና እውነት አድርገው ስለወሰዱት ስድብን አስቀድመው አመክንዮአቸውን
አስከትለው አቅርበዋል፡፡ ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን ብለው ሲያበቁ ምክንያታቸውንም አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም …በውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ ራስህን ማንን
ታደርጋለህ? ይሉታል፡፡ ጌታችንም አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ አየም ደስም አለው
ባላቸው ጊዜ አይሁድ ገና ሃምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን?
ብለውታል፡፡ ጌታችንም እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ ብሎ ትክክለኛ ማነነቱን ቢነግራቸው ከአመክንዮአቸው
የሚልቀውን እውነት ላለመቀበል ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፡፡
ይህንን የመሰሉ ክርስቶስን የተመለከቱ የማንነት ጥያቄዎች በቅዱስ
መጽሐፍ በርካታ ጊዜ ተነስተዋል፡፡ ክርስቶስ አንተ ነህን ንገረን
ሉቃ.22፣67፤ ዮሐ.10፣24፤ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል ማር.2፣7 የሚሉትን መመልከት
ይቻላል፡፡
የማንነት ጥያቄ ታልቅ ከመሆኑ የተነሳ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
በኦርቶዶክሳዊነታቸው የምትቀበላቸው ሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ማለትም ጉባኤ ኒቂያ፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ እና ጉባኤ ኤፌሶን የማንነት
ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጠሩ ነበሩ፡፡ በጉባኤ ኒቂያ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ተነስቶ ከአብ ጋር አንድ የሆነ አምላክ፣ በጉባኤ
ቁስጥንጥንያ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ተነስቶ ከአብ የሰረጸ አምላክ፣ በጉባኤ ኤፌሶን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል ማርያም
ማንነት ተነስቶ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ የሚሉ ምስክርነቶች ከቅዱሳት መጻሕፍት በመሰጠቱ እና ይህንንም እውነታ በውሳኔ በማጽናታቸው
ነው፡፡
የአይሁድ
ስሕተት
አዋቆች ነን ባዮቹ ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያን በአጠቃላይ
አይሁድ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት መሰረታዊ ስህተት ውስጥ የወደቁት ከሚያጣቅሷቸው መጻሕፍት አግባብ አለመሆን አልነበረም፡፡
ነገር ግን በእነርሱ ዘንድ ያለውን በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን እውነታ አንድም በአግባቡ ባለመረዳት አንድም ለራሳቸው ምድራዊ
ክብር በሚያመች ሁኔታ ሲተረጉሟቸው ስለ ነበር ነው፡፡ ጌታችንንም ጋኔን
ያለበት፣ የዮሴፍ ልጅ፣ ኃጢአተኛ …በሚሉ አይደለም ለክርስቶስ
ለአንድ ተራ ሰው እንኳ ቢቀጸሉ ተገቢ ያልሆኑ አገላለጾችን ተጠቅመው ጠርተውታል፡፡ ይሁንና ጌታችን ይድኑ ዘንድ እውነቱን አብዝቶ
ነገራቸው እንጂ አላራቃቸውም፡፡ እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለሆንሁ አታምኑኝም ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ
እናንተ ስለምን አታምኑኝም? እንዲል ዮሐ.8፣45-46
ደግሞም እኔስ ጋኔን የለብኝም… እናንተም ታዋርዱኛላችሁ ብሏል፡፡
ቁ.49 ከሁሉ አስቀድሞ በብዙ መንገድ ለድኅነት የተጠሩት አይሁድ ቢሆኑም ስለ ክርስቶስ ማንነት ሳይረዱ ቀርተው ከፊሎቹ ከተስፋው
ወጥተዋል፡፡
አረዳዳቸውና ድርጊታቸውም ራሱ ዕውር ሆኖ ብርሃንን የሚሻውን
ዕውርን እንምራህ እያሉ ተያይዘው ገደል ገብተዋል፡፡ ማቴ.15፣14 በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈውም እውነትን ከመረዳት
ውጭ ሆነው ስለ ክርስቶስ ማንነት መረዳት ተስኗቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ጌታችን እንዲህ አላቸው እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ
ናቸው ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ዮሐ.5፣39-40
በዚህ በዘመናችንም በእነርሱ ዘንድ እውነት እንደሌለ ቢያውቁት
ሳይጠሯቸው እና ሳያገባቸው እናት ያልሆነቻቸውን እውነት የያዘችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን እናድሳት እያሉ በከንቱ ይቀባጥራሉ፡፡ በእውነት ክቡር ሆኖ የተፈጠረ የሰው ልጅም እንዲህ ባለ ከንቱ ስራ ሲሰማራና
በግድ ጨምሩኝ ብሎ በሌለው እውነት፣ ሊቅነትና ቅድምና ሲዳክር፣ ምእመናንን የዲያብሎስ ምርኮኛ ሀገርን ዘመናዊ ቅኝ ተገዢ እንድትሆን
ሲሰራ ማየት ያማል፡፡ ለመዳን ጨምሩኝ ብለው ቢሆንስ ባልከፋ የቤተክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ለድኅነት መጥራት ነውና፡፡ ነገር ግን
እነርሱ የአባታቸው የዲያብሎስ ደቀመዛሙርት ሆነው ክርስቶስ ራሷ የሆነውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ይታገላሉ፤ ለዚህም ነው ሰልፉ
መንፈሳዊ ሰልፍ የሚሆነው፡፡
“በአንድ ቤተ እምነት ተግኝቶ አንድ ሰው የተናገረው” በሚል
ነጣቂ ተኩላነታቸውን በመመስከር በተሐድሶ መጽሔት ላይ የሰፈረው “…ከእንግዲህ
ሰውን ከዓለም እንጂ ከቤተ ክርስቲያን አናወጣም፡፡ ወደ ጤናማነት እንመለሳለን እንጂ ከእንግዲህ ወደ እብደት አንሄድም፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን የሚልበትን አስተሳሰብ ስንመለከት
በአንድ በኩል “ሁሉም አብያተ እምነት ያድናሉ” ከሚል አደገኛ እና ፈጽሞ ስሑት የሆነ አስተሳሰብ ሲሆን በሌላ በኩል ደግም በየቤተ
እምነታቸው እንዳሉ ሆነው መርዛቸው እንዲረጩ በማሰብ መሆኑን ያስታውቃል፡፡ “ከሌላው የተነጠቁ ምእመናን ሁሌም የእናንተ አይደሉም፤
የዚህ ሰው ፈውስ ያለው በቤተ ክርስቲያኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሙሉ ወንጌል የሆነውን ወደ ሙሉ ወንጌል፣ መሠረተ ክርስቶስ የሆነውን ወደ
መሠረተ ክርስቶስ፣ ኦርቶዶክስ የሆነውን ወደ ኦርቶዶክስ(መልሱ)… አዎን የክርስቶስ ኢየሱስን ሥራ እዚያ በስፍራቸው ሆነው ያቀጣጥሉ፡፡”
ኆኅተ ብርሃን መጋቢት 2002 ገጽ 4
kalehiwot yasemalin
ReplyDelete