Monday, February 26, 2018

የአመክንዮ አቅም (ክፍል ሦስት-የመጨረሻው)


የእውቀት መገለጫ
በእምነት ይገኛል
1ኛ ቆሮ. 2፣14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡ መንፈስ የሆነን ነገር በአመክንዮ ብቻ ለሚመረምረው ሰው ሞኝነት ይመስለዋል፡፡

አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂዶ ድንጋዩን ሲሳለም፣ ቅዱሳት ስዕላቱን ሲተሻሽ አምላከ ቅዱሳን ማረኝ ሲል፣ ቅዱሳንን አማልዱኝ ሲል በሥጋዊው ሰው እይታ ሞኝነት ይሆንበታል፤ በአመክንዮ ከሚገኘው እውቀት በላይ ሌላ እውነት የሌለ ስለሚመስለውና አመክንዮም ከአቅም ማነስ የተነሳ ወደዚህ እውነት ከመድረስ ስለምትከለክለው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በእምነት ለሚመረምረው ሰው ይህ የተለየና ከአመክንዮ በላይ ካለው እውነት ጋር መገናኘት እንደሆነ ይረዳዋል፡፡  እውነተኛ የሆነው እውቀት ከእምነት በኋላ የሚመጣ ነው፤  እውነተኛ እውቀት እምነትን ይፈልጋልና፡፡ እውነተኛ እምነት ያለውም ሰው እውነተኛ እውቀትን ያገኛል፡፡

በፍልስፍና እውነተኛ እውቀትን አንደርስበትም፡፡ በፈላስፎች ዘንድ እጅግ አዋቂ እንደሆነ የሚታመነው የግሪኩ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ተይዞ ለሞት በቀረበበት ጊዜ በመጨረሻው ሰዓት እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ የመሰናበቻው ሰዓት ደርሷል፤ እኛም የየራሳችንን መንገድ እንጓዛለን፤ እኔ ወደ ሞት እናንተም ደግሞ ወደ ሕይወት ከሁለቱ ግን የትኛው እንደሚሻል ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ የለም፡፡

ስለዚህ ሶቅራጥስ የሰው ልጅ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ነው የሚሻለው ወይስ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ቢቆይ የሚለውን የሰው ልጅ መርምሮ ሊደርስበት ወይ ሊያውቀው አይችልም በማለት የሰው ልጅ የማይደርስባቸው እውቀቶች እንዳሉ ተናግሮ አልፏል፡፡ በሃይማኖት ግን ይህ ጥያቄ መልስ አለው፡፡

ዮሐ. 5፣28 በመቃብር ውስጥ ያሉት ድምጹን የሚሰሙበት ጊዜ አለና በዚህ አታድንቁ እንደተባለ ስለዚህ ሙታን ይነሳሉ በማለት ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ፣ እናም ሶቅራጥስ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው ያለውን እውቀት መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ያን እውቀት በግልጽ ለይቶ ይነግረናል፡፡

 በማቴ.25፣ 35 ስለ ትንሳኤ ሙታን እና ዘልዓለማዊ ፍርድ በግልጽ ሲያስረዳ መልካም የሠሩ በክብር ትንሳኤ የሚነሱት ወደ እኔ ኑ ሲባሉ ክፉ የሠሩ በውርደት ትንሳኤ የሚነሱት ከእኔ ራቁ የሚባሉ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ስለዚህም በፍልስፍና ሳይሆን በእምነት ወደ እውነተኛው እውቀት እንደርሳለን፡፡

የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት መልስ ያገኘው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመግለጡ፡፡ በሌላ መንገድ በፍልስፍና ልናውቀው አንችልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ፣ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ፣ ከባሕርይ አባቱ ከአብ እንደሚወለድ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይበልጥና ሳያንስ እንደሚገናዘብ… ልናውቀው የምንችለው በእምነት ብቻ ነው፡፡

እውነተኛ አውቀት መሰረቱ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ በአሁኑ በዘመናችን የጌታችንን ማንነት በተመለከተ ትክክለኛውን መልስ በማግኘትና ባለማግኘት የተከፈሉ ብዙ አመለካከቶችን እናገኛለን፡፡ እውነተኛው ማንነት የሚገኘው ግን በእምነት መሰረትነት ነው፡፡ 

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 119፣66 ላይ በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ በማለት ከማወቅ ማመን መታመን እንደሚቀድም እና ለማወቅ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡ በ2ኛ ነገ.6፣17 የሶርያ ንጉስ በእስራኤል የሚመክረውን የጥፋት ሐሳብ አስቀድሞ በማወቅ ድል እንዲሆን ያደርግ የነበረውን የእግዚአብሔርን ነቢይ ኤልሳዕን ይዘው እንዲያመጡለት ሰራዊቱን በላከ ጊዜ የነቢዩ አገልጋይ የነበረው ጊያዝ ማልዶ ሲነሳ የከበበውን አስፈሪ ሰራዊት አይቶ መምህር ሆይ ልንጠፋ ነው ባለ ጊዜ ነቢዩ አቤቱ የባርያህን ዓይኖች እንዲያዩ አድርግ ብሎ ጸለየ፡፡ የጊያዝ ዐይኖች የሶርያ ንጉሥ ሰራዊቶችን አይተዋል፤ ይህ ለሁሉም የሚታይ፣ ማንም ሰው በስሜት ሕዋስ በአመክንዮ የሚደርስበት፣ ፊት ለፊት የሚታየው እውቀት ነው፡፡ ነቢዩ የጸለየው ግን አገልጋዩ በዐይኑ ከሚያየው ባሻገር ሊያየው ያልቻለው ነገር ግን ከሚያየው ሌላ  ያላየው እውነታ ስላለ ነበር፡፡

ጊያዝም ዐይኖቹ በተገለጡ ጊዜ በኤልሳዕና በጊያዝ ወገን የቆሙ አስቀድሞ ከፈራቸው የሶሪያ ንጉሥ ሰራዊቶች ይልቅ የሚበዙና የሚያስፈሩ የእሳት ሰረገላ ያላቸው ሰማያውያን ሰራዊት ከብበዋቸው አይቷል፡፡ ስለዚህ ሰው በእምነት ሲያውቅ እና ያለ እምነት ሲያውቅ ልዩነት አለው፡፡ ያለ እምነት ሲያውቅ በሰሜት ሕዋስ ሊረዳው የሚችለውን ያህል ይረዳል፤ በእምነት ሲያውቅ ደግሞ እውነታው ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፡፡ ስለዚህም እውቀት እምነትን መሰረት ያደርጋል፡፡ 

መጠን አለው
አንድ ሰው ሁሉንንም ነገር አውቆ ሊዘልቀው አይችልም፡፡ የሰው ልጅ እግዚአብሔር በረዳውና በገለጠለት መጠን እንደ እምነቱ ያውቃል፡፡ ነገር ግን እውቀትን በሙሉ በፍጹም የሚያውቅ ፍጹም የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ለእግዚአብሔር የምንተዋቸው እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ መረዳቶች፣ እውቀቶች አሉ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛ ቆሮ.13፣9 ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን እንዳለ ሁሉንንም እውቀት መርምረን አንደርስበትም፡፡ ምድር ስንት ጥቃቅን ነገሮች አሏት? የጸጉራችን ብዛት ስንት ነው? ብለን ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን እንኳ ብንጠይቅ የሰው ልጅ መልስ ማግኘት ይቸገራል፡፡ የሰው ልጅ አእምሮ የማይደርስባቸው በተደሞ በአንክሮ ሊያያቸው የሚገቡ ዕጹብ ድንቅ ሊላቸው የሚገቡ ብዙ እውቀቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከእውቀት ከፍሎ ሊያውቅ ይችላል እንጂ እውቀትን ፈጽሞ ጠንቅቆ ማወቅ አይችልም ፍጹም የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ፡፡ ሉቃ.10፣22 ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም ይላል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ማወቅ የሚቻለው በተገለጠው ልክ ነው እንጂ ጠንቅቆ ማወቅ አይቻልም፡፡

እውቀት በልክ ነው፡፡ አንድ ሰው ሁሉንም ነገር ልወቅ ብሎ ቢነሳ ሊሆንለት አይችልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በፈቀደለት ልክ ማወቅ ይገባዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በከንቱ እንድንኖር የሚያደርጉን፣ ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ፣ ምናልባትም ለድኅነታችን ፋይዳ የሌላቸው፣ ፋይዳ ቢኖራቸውም እንኳ ልንድርስባቸው የማንችላቸውን ነገሮች ለአግዚአብሔር መተው ያስፈልጋል ለእግዚአብሔር የምንተዋቸው እውቀቶች አሉና፡፡

ቅዱስ ሄሬኔዎስ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ምን ሲሠራ ነበር ? ብሎ አንዱ ቢጠይቅ መልሱ በራሱ በእግዚአብሔር እጅ ብቻ ነው ይህ በመጻሕፍት አልተገለጠምና ወደ ስህተት እንዳናመራ እንዲህ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለእግዚአብሔር መተው አለብን ይለናል፡፡

በፍልስፍናው መንገድ የእውቀትን ውሱንነት በተመለከተ ኖውሌጅ ስኬፕቲሲስዝም የሚባል አለ፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል እውነተኛን እውቀት የሰው ልጅ ሊደርስበት አይችልም የሚሉ የተለጠጠ አስተሳሰብ ሲያራምዱ በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ እውተኛ እውቀትን ሊደርስበት ይችላል ነገር ግን እርሱን ማረጋገጥ አይቻልም የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ በፍልስፍናውም ቢሆን ፍጹም እውቀት ከሰው ልጆች ጥበብ የራቀች እንደሆነ የሚጠቁም ነገር አለ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እውነተኛ እውቀት የምናገኘው/የሚገለጥ እንጂ በሰው ልጅ ምርምር የምንደርስበት እንዳልሆነ ተገልጧል፡፡

በሌላ በኩል እውቀትን ብቻ ይዞ መጓዝም በብዙ መልኩ ስህተት ውስጥ የሚጥል ሲሆን በተለይ ደግሞ በትዕቢት እንድንጣል ያደርጋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.8፣10 እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል እንዲል፡፡ ቀሌሜንጦስ ዘሮም በመልእክቱ እውቀት በአመክንዮ ሂደት  በማሳያ/ዲሞንስትሬሽን ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ የሚናገር ሰው መርሆዎች በማሳያ ማለፍ የማይችሉ መሆናቸው በመጀመሪያ ይስማ እነርሱ በኪነጥበብም ሆነ በመልካም ፍርድ የሚታወቁ አይደሉምና፡፡ ኋለኛው የሚለዋወጡ ነገሮች ማወቂያ ነውና የመጀመሪያው ግን ክልስ ሐሳባዊ ሳይሆን ተግባራዊ ብቻ ነውና፡፡ ይላል፡፡ (እምነት የሁሉም እውቀት መሰረት-ምዕ.4)

ዮስጢኖስ ሰማዕትም እንዲህ ይላል፡፡ ስለዚህ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት እና ስለራሱና ስለሌሎች ሁሉም ነገሮች ማረጋገጫ ነው፡፡ እምነትን ማረጋገጫቸው አድርገው እርሱን የሚከተሉትና የሚያውቁት በእርሱ ዕረፍትን ያገኛሉ፡፡ (በእንተ ትንሳኤ- የእውነት ራስን የማረጋገጥ ኃይል)


ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።