Friday, April 8, 2016

ጥያቄና መልስ



መጠየቅህ ላይቀር እግረ መንገድ አትጠይቅ፤ አስበህበት ጠይቅ፤ እውነተኛ መልስ ለማግኘት የእውነት ድከም፤ እግረ መንገድ እየጠየቅህ እግረ መንገድ አትኑር፤ እንደ ሐዋርያትየእውነት ጠይቀህ የእውነት ኑር። ስትጠይቅ የእውነት ጥያቄ ሆኖብህ፣ አሳስቦህ፣ ለድኅነት ፈልገከው ከሆነ መልሱን ለማግኘትም ለማጣትም የእውነት ድከም፤ ሳትፈልገው አጣሁት  ሳትረዳውም አገኘሁት አትበል።

ለጥያቄህ አንደበት ለመልሱም ጆሮ ይኑርህ።
የሚጠይቁትን ባለማወቅ አይደለም መልሱ ጥያቄው ራሱ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ የሚሳናቸው አሉና፤እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችም ለጥያቄው መልስ በማጣት ሳይሆን ራሱን ጥያቄውን በማጣት ይቸገራሉ።
ጥያቄዎቻቸውን በብዙ ሕብረ ቀለማት እየቀቡ በራሳቸው በጥያቄዎቹ ከሚመኩባቸው በላይ በጥያቄዎቹ ላይ ባኖሯቸው ሕብረ ቀለማት እየተማረኩ ለመልሶቹ ጆሮ መስጠት የሚያዳግታቸው፣ የጥያቄ ጀግኖች ሆነው መኖርን፣ምላሽ የታጣባቸውን ጥያቄች ፈጣሪዎች መሆንን እንጂ መልስ ፈላጊዎች መሆንን የማይሹም አሉ።

መጠየቅ ነውር የሚመስላቸው ወገኖች አሉ።ይህ ሁለት ገጽታ ሊኖረው ይችላል በአንድ በኩል ብጠይቅ መዳፈር ይሆንብኛል በሚል በሌላ በኩል ብጠይቅ መልስ አላገኝበትም በሚል፤ ብጠይቅ መዳፈር ይሆንብኛል ብለው ከመጠየቅ የሚቆጠቡት ሰዎች የእግዚአብሔር ታላቅነት ጎልቶ የሚታያቸው ሲሆኑ ከኃያልነቱ የተነሳ እና/ወይም ከፍቅሩ የተነሳ ጠይቄ ኃያልነቱን ከምፈታተን እና/ወይም ፍቅሩ ከሚጎድልብኝ ፣በመጠየቄ በሐሳቤ ከሚመላለሱ አስተሳሰቦች የተነሳ ከማሳዝነው ሳልጠይቅ ቢቀርብኝ ብለው በጥያቄአቸው ላይ የሰለጠኑ፣የመጠየቅ መብታቸውን በመተው፣ ጥያቄአቸውን በመገደብ ራሳቸውን መስዋዕት የሚያደርጉ ናቸው።

ብጠይቅ መልስ አላገኝበትም የሚለውም ሁለት ገጽታ ሊኖረው ይችላል አምኖ ማብራሪያ የሚፈልግ ሰውና ሳያምን ለማመን ማብራሪያ የሚፈልግ ሰው። አምኖ ማብራሪያ የሚፈልግ ሰው ጥያቄው እንዲመለስለት ይፈልጋል፤ ማብራሪያ እንዳለውም እርግጠኛ ነው። ነገር ግን በአግባቡ የተማረ እና መልስ ሊሰጠው የሚችልን ሰው እስኪያገኝ ድረስ መታገስን እንደ ተጋድሎ ይወስደዋል። ሳያምን ለማመን ማብራሪያ የሚፈልግ ሰው ደግሞ መልስ አሁኑኑ ያስፈልገዋል ካላገኘ አያምንም፤ ካገኘ ያምናል።

መጠየቅ በራሱ ኃጢአት አይደለም። እንዲያውም የእውነተኛ አማኝ ማሳያ ሊሆን ይችላል።  በእውነተኛ ሃይማኖት ለሚኖር ሰው፡ አለመጠየቅም በራሱ ኃጢአት አይደለም፤ እንዲያውም የእውነተኛ አማኝ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

No comments:

Post a Comment

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።