Wednesday, July 29, 2015

ምዕራፍ ሁለት- ትንሣኤ የማይቻል አይደለም



       እንግዲያው የትንሣኤን ጉዳይ እኔ እንዳመለከትኩት እንየው፤ አለማመን ሁሉ ከፌዘኝነትና ከቸልተኝነት የሚነሳ ካልሆነ፡ ነገር ግን ከአንዳንዶች አዕምሮ ከጠንካራ አስተሳሰብ የሚመነጭና ለእውነት በሚገባ እርግጠኝነት የተደገፈ ከሆነ  መልካም ነው፤ ከእነርሱ አለማመን ጋር የተዛመደው ይህ ነገር በራሱ ለእምነት የማይጠቅም ሆኖ ከታያቸው ሚዛናዊ መሆንን ያስጠብቃል፤ ነገር ግን ሊካዱ የማይገባቸውን ነገሮች መካድ ስለ እውነት ጠንካራ ፍርድን ማኖር የማይችሉ ስዎች ተግባር ነው፡፡
    ስለዚህ እነዚያ ትነሣኤን በተመለከተ የማያምኑ ወይ የሚጠራጠሩ የራሳቸውን አመለካከት ለመፍጠር በችኮላ ከተቀበሉት ማንኛውም እይታ ሳይሆን እንዲሁም ሰዎችን ቸልተኛ ከማድረግ ሳይሆን ነገር ግን የሰዎች መገኛ ያለ ምክንያት ነው ለማለት ወይም የነገሮችን ሁሉ ምክንያት ለእግዚአብሔር በመስጠት በዚህ የእምነት ርእስ ላይ ያለውን መርሕ በዝግታ ለመጠበቅ ከዚህም በመነሣት ትንሣኤ ፈጽሞ የሚሆን እንዳልሆነ የመግለጽ ሓላፊነት አለባቸው፤ እነርሱ ለእግዚአብሔር ትንሣኤ የማይቻል መሆኑን ማሳየት ከቻሉ ወይ ትነሣኤ  የሞቱ ወይም ወደ ክፍልፋይነት የተበታተኑ ሰውነቶችን እንደገና አንድ ዓይነት ማድረግ እና መሰብሰብ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃራኒ መሆኑን ማሳየት ከቻሉ ይሳካላቸዋል፡፡ እነርሱ ይህን ማድረግ ካልቻሉ እንግዲያውስ ከዚህ እግዚአብሔር የለሽ አለማመን እና ምስጢራዊ ነገሮችን ከመዳፈር ያቁሙ፤ እነርሱ ትንሣኤ አይቻልም ወይም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አይሄድም ሲሉ አውነትን እንደማይናገሩ እኔ ቀጥዬ ከምለው በግልጽ ይታያልና።
   አንድ ነገር ለሰው ፈጽሞ የማይቻል ነው የሚባለው እርሱ ምን እንደሚሠራበት (ሠ- በማጥበቅ ይነበብ) የማያውቅ ከሆነ ወይም የሚታወቀውን ነገር በአግባቡ ለማከናወን በቂ ኃይል /ሥልጣን ከሌለው ነው፡፡ መሠራትን(ሠ- በማጥበቅ ያንብቡ) ስለሚፈልግ ነገር ምንም ዕውቀት የሌለው ሰው ዕውቀት አልባ የሆነበትን ነገር መሥራት ወይ መሞከር ፈጽሞ አይችልም፡፡ እንዲሁም ምን በምን እና እንዴት እንደሚሠራ አሳምሮ የሚያውቅ ነገር ግን  ምንም ኃይል የሌለው ወይ በቂ ኃይል የሌለው ሰው ጥበበኛና ኃይሉን ያገናዘበ ከሆነ ሙከራውን እንኳ አያደርግም፡፡ እንዲሁም በጥልቀት ባለማሰብ ከሞከረው ዓላማውን አይፈጽምም፡፡
   ምንም እንኳ  በተፈጥሮው መሠረት  ከዩንቨርስ ጋር የተዋሐደውን እንደገና መለየት ለሰዎች ፈጽሞ የማይቻል መስሎ ቢታይም ነገር ግን  ስለሚነሱ ሰውነቶች ተፈጥሮ (ስለ አጠቃላይ አካላት ስለያዟቸው ነገሮች) ወይም እያንዳንዷ የሟች ነገር የምታልፍ መሆኗን ከአካሎች ምን እንደተቀበለችና አብሯት ወዳለ ምን እንደተላለፈ   አላዋቂ መሆን ለእግዚአብሔር አይቻልም፡፡
ከቀድሞ እንግዳ የሆኑትን የሰዎች ሰውነት ሊይዛቸው ስለ ሚገቡ ነገሮች ተፈጥሮ   ወይም ለሰው ልጅ ሰውነት መሠራት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ነገሮች ስለሚወስድባቸው አካላት የተሰወረበት ካልነበረ ሁሉም ካለፈ በኋላ እያንዳንዷን አካል ለማዘጋጀት ስለተጠቀመባት እያንዳንዷ ነገር ሕልፈት አላዋቂ አይሆንም። በኛ ዘንድ ከሚገኙት ነገሮች ስርዓት አንጻር እና እኛ ስለ ሌሎች ነገሮች ከምንሰጠው ፍርድ  አንጻር ከተመለከትነው ሕልፈት ስላላገኘው ነገር ቀድሞ ማወቅ ትልቅ ነገር ነው፤ ከእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ አንጻር ካየነው ግን ሁለቱም ያልሆኑ ነገሮችን እንደሚሆኑ ቀድሞ ማወቅና ሆነው ያለፉ ነገሮችን ማወቅ እኩል ቀላል ናቸው።
አቴናጎራስ

የአቴናጎራስ ሥራዎች



      ሄርማስ፡ታትያን፡ቴዎፍሎስ እንዲሁም ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ በነበሩበት ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ ተብሎ በሚታወቀው ዘመን የነበረ ክርስቲያንና ፈላስፋ ነው አቴናጎራስ፡፡ ከዚህም ሌላ አርጌንስና ጠርጡለስ በነበሩበት የሁለተኛ መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳ ፍቱን ብዕርና የዳበረ አዕምሮ የነበረው ሰው ነው፡፡
      ስለ አቴናጎራስ የሚያወሱ ሁለት የጥንት ቤተክርስቲያን መዛግብት ብቻ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም፤
  •   ኤጲፋንዮስና ፎጢኖስ መዝግበው ባስቀመጡት ስለ ሰውነት ትንሣኤ በሚናገርው በሜቶዲየስ በተዘጋጀው ጽሑፍ ላይ
  •   በፓምፊሊያ ባንጸባረቀው ፊሊጶስ ዘሲዴ በጻፈው ላይ ናቸው፡፡
      አቴናጎራስ አስቀድሞ የአቴና ፈላስፋ ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመንቀፍ ሲያነብባቸው በትምህርታቸው ተስቦ ክርስቲያን እንደሆነ ፊሊጶስ ዘሲዴ ጽፏል፡፡
      አቴናጎራስ ብዙ እንደጻፈ ቢታመንም አሁን ድረስ ተጠብቀው ያሉ ስራዎቹ ግን ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ስለ ክርስቲያኖች የጻፈው የጥብቅና ጽሑፍና ስለሙታን ትንሣኤ የጻፈው ናቸው፡፡ አቴናጎራስ ባለ ብሩህ አዕምሮ፣የዳበረ ልምድ ያለው ጸሐፊ፣ ጥልቅ ነገርን በሚገባ(ለመረዳት በሚያስችል) መልኩ መጻፍ የሚችል፣ ታዋቂ ከሆኑ ከጥንት የቤተክርስቲያን ጠበቆች አንዱ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚመሰከርለት ነው፡፡
      ስለ ክርስቲያኖች የጻፈው ጥብቅናው በሰላሳ ሰባት ምዕራፎች፣ ስለሙታን ትንሣኤ የጻፈው ደግሞ በሃያ አምስት ምዕራፎች ተከፋፍለው ይገኛሉ፡፡
      በጥብቅና ሥራዎቹ ውስጥ ትኩረት የሰጣቸው ጉዳዮች፡ በክርስቲያኖች ላይ ስለሚነሱ ክሶች የአግባብነት ጉድለቶች፣ ስለሚሰጣቸው ኢ-ፍትሐዊ ፍርድ፣ ስለሚፈጸሙባቸው አድሎዎች፣ ስለ ክርስቲያኖች ሞራላዊ ልዕልና፣ በክርስቲያኖችና በከሳሾቻቸው መካከል ስላለው ሰፊ የሞራል ልዩነት፣  በአንድ አምላክ ማመን፣ በአንድ አምላክ ስለ ማመን የባለ ቅኔዎችና የፈላስፎች ዕይታዎች፣ ሐሰት ስለሆኑ የጣኦቶች አምልኮዎች የሚሉ ይገኙበታል፡፡
      የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ በጻፈው ጽሑፉ ውስጥ ትንሣኤ የሚቻል እንደሆነ፣ ልዩ ልዩ የትንሣኤ ምሳሌዎች፣ በትንሣኤ ጊዜ ስለሚኖረን ሰውነት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
      ከዚህ ቀጥሎ ከትንሣኤ ሙታን ጽሑፎቹ ውስጥ የተወሰኑት እንደሚከተለው ተተርጉመው ቀርበዋል፡፡  

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።