(ክፍል፪)
የተከበራችሁ አንባቢያን ከወራት በፊት ታላላቆች ፊደላት በሚል ርእስ
በተጀመረው ጽሑፍ የተወሰኑት ታላላቆች ፊደላት ከዚህ ክፍል ጀምሮ ይብራራሉ።
ጠላትነትን አደርጋለሁ ዘፍ.፫፡፲፭
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተወሱት ታሪኮች የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር መለየት ቀዳሚው ነው። እግዚአብሔር
አምላክ የፍጥረታት አምላክ ነውና ፍጥረታቱን ያዝዛቸዋል። ፍጡራን ፈጣሪያቸው ለምን እንደሚያዝዛቸው ቢያውቁም ባያውቁም የእግዚአብሔርን
የባህርይ አዛዠነት፣ የፍጡራንን ታዛዠነት አይቀይረውም። ይህም ማለት ፍጥረታት በፈቃዳቸውም ሆነ ካለፈቃዳቸው ለፈጣሪያቸው ይታዘዛሉ
ማለት ነው። ከፍጡራን መካከል ለብዎ (ልብማድረግ) ያላቸው ሰዎችና መላእክት ወደው ሲታዘዙት በረከትን ሲያገኙበት፣ ሳይወዱ ሲታዘዙት
ቅጣትን ይቀበሉበታል። አብርሃምና ይስሐቅ ከሰዎች፣ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ከመላእክት ወደውና ፈቅደው ለበረከት የታዘዙት
ምሳሌዎች ሲሆኑ፤ ንጉሠ ባቢሎን ናቡከደነፆርና (እስራኤልን ሲማርክ) ዲያብሎስ (ነፍሳት ከሲኦል በወጡ ጊዜ) ደግሞ ሳይፈቅዱ ለቅጣት
የታዘዙት ምሳሌዎች ናቸው።
እንግዳ ትምህርት
“እባብም እግዚአብሔር አምላክ
ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ።”ቁ.፩ እባቡ እግዚአብሔርምን ብሎ እንዳዘዛቸው ማረጋገጥ በሚፈልግ ሁናቴ ሄዋንን
ጠየቀ፤ የሄዋን መልስ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በአዘዘው መሠረት እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ ብሎናል የሚል ነው።
አስቀድሞም ለመረዳት ሳይሆን ለመርታት፣ በመጠየቅ ለማስጠየቅ የተጀመረው የእባብ አካሄድ
ከጠያቂነት ወደ መላሽነት፣ ከመማር ወደ ማስተማር ተሸጋገረ። እናም በድፍረት እግዚአብሔር ያላስተማረውን፣ በአዳምና በሄዋን ልብ
ያልተጻፈን እንግዳ ትምህርት አስተማረ።
እግዚአብሔር ያላሰማራቸው ፣መንፈስ ቅዱስ ያላደረባቸው፣ ቅድስት ቤተክርስቲያን ያልላከቻቸው
እንግዳ ትምህርት፣ እንግዳ ስርአት፣ እንግዳ ዜማ የሚያመጡ የዘመናችን ሰዎች በማወቅም ባለማወቅም የእባቡ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን
በተግባር ይመሰክራሉ። እግዚአብሔር በልቡና ሳይጽፈው፣ በሕሊና ሳያሳድረው ከራሱ አንቅቶ እንግዳ ትምህርት የሚያመጣ እባቡ ነውና።ዮሐ.፰፣$፬
ማረጋገጫ
የሌለው፣ አስቀድመን ከምናውቀው ሌላ የሆነ፣ ከእውነተኛይቱ ትምህርት የሚያርቅ እንግዳን ትምህርት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እንሰማ
ዘንድ እንጂ እንቀበል ዘንድ የግድ አይደለም። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‘’ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ።’’
ሲል መምከር አስፈለገው።ዕብ.፲፫፣፱
የተከፈቱዐይኖች
“የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን
እንደሆኑ አወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።” ቁ.፯
ይህ የሆነው
አዳምና ሄዋን በእንግዳ ትምህርት ተወስደው እፀ በለሷን ከበሉ በኋላ ነው። አዳምና ሄዋን አስቀድመው ዐይኖቻቸው ኃጢአትን እንዳያዩ፣
ወደ ኃጢአት እንዳይሳቡ በጸጋ እግዚአብሔር ተጠብቀው ነበር። ይሁንና ጸጋውን ትተው በጸጋው ፋንታ ዕውቀታቸውን፣ አስተሳሰባቸውን
በመምረጣቸው እንደ ዕውቀታቸው መጠን፣ እንደ አስተሳሰባቸውም መጠን ወደቁ፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ከሰው ልጅ ዕውቀት እና አስተሳሰብ፣
የእግዚአብሔርም ሞኝነት ከሰው ልጅ ጥበብ ይልቅ ይበልጣልና።፩ቆሮ.፩፣፳፭
በዚህም
መሠረት ከውድቀት በኋላ አዳምና ሄዋን ራቁታቸውን እንደሆኑ የሚያውቁበት፣ የሚተፋፈሩበት ዕውቀት ያገኙ ዘንድ ዐይኖቻቸው ተገለጡ።
ኃጢአትን ስናደርግ እግዚአብሔርን የምናይባቸው ዐይኖቻችን ሲከደኑ፤ ዓለምን የምንከተልባቸው ዐይኖቻችን ይገለጣሉ። የእግዚአብሔር
ጸጋ ሲርቅ ባዶነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ዝሙትን ራስን መውደድ ሌላውን ለመጉዳት በማሤር በአጠቃላይ የኃጢአት መንገድ፣ ራስን ማጥፋት
ይከተላል። ስለዚህም መዳንን ለሚሻ ለሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ጸጋ፣ እውነተኛ ሃይማኖት መያዝ ብቸኛ እንጂ አማራጭ አይደለም።
ጠላትነት ለወዳጅነት
ከዚህ
በኋላ እግዚአብሔር አስቀድሞ በሰጠው ትእዛዝና ትእዛዙን የመጠበቅና ያለመጠበቅ ውጤት መሰረት በአዳምና ሄዋን ላይ ፈረደባቸው። እባቡንም
እንዲህ አለው። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን
ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”ቁ.፫፣፲፭
በቅዱስ
መጽሐፍ ዲያብሎስ የቀደመው እባብ ተብሎ ተጠቅሷል።ራዕ.20፣2
ስለዚህም አዳምንና ሄዋንን አሳታቸው የተባለው በእባብ ላይ ያደረው ዲያብሎስ ነው። በአንተና በሴቲቱ መካከል ማለቱ በዲያብሎስና በሄዋን መካከል፣ በዘርህና በዘርዋ መካከል ማለቱምም በዲያብሎስ ዘር (የዲያብሎስን ክፋት በያዙ አይሁድና በራሱ በዲያብሎስ) እና
በሄዋን ዘር (ከሄዋን ዘር ከእመቤታችን-/የትውልድ ሃረጓ ከመጀመሪያው አባት አዳምና ከመጀመሪያዋ እናት ሄዋን ነውና/ በተገኘው)
በክርስቶስ መካከል ጠላትነትን እንደሚያደርግ ተናገረ። ስለዚህም እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ በቀራንዮ በመሰቀል ዲያብሎስን ፈጽሞ
ተጣላው (ድል አደረገው)። በዚህም በዲያብሎስ ዘርና በሄዋን ዘር መካከል ጠላትነትን በማኖር ከእርሱ ጋር ወዳጅነትን እንድንመሰርት
አደረገን። በፈራጅነቱ እየቀጣን (አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ…) በመሐሪነቱ አዳነን። በዚህም የድኅነትን ውል ገባልን። እናም
ከዲያብሎስና አጋሮቹ መናፍስት ጋር መጣላት ከእግዚአብሔርና ባለሟሎቹ ቅዱሳን ጋር መታረቅ ነው። ዲያብሎስን መጣላት ማለትም ስራውን
አለመከተል፣ ትምህርቱን አለመቀበል፣ እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት ሲሆን ዲያብሎስን “እክህደከ” ማለት እግዚአብሔርን “አአምን ብከ”
ለማለት ነው።
እግዚአብሔር አገልግሎህን ይባርክልህ። እጅጉን በጣም አስተማሪ ነው። አሁንም ብዙ ነገር ካንተ እንጠብቃለን።
ReplyDelete