(ዮሐ.19፣22)
የፍርድ ቤቱ ውሎ የተዛባና የሚያበሳጭ ነበር፡፡ የከሳሽ ጩኸት ከፈራጅ እውቀትና አመክንዮ ይልቅ ገዝፎ፣ ፍርድ ከእውነት
ሚዛን ወጥታ ዛቻንና ማስፈራርያን ለማከም ስትል በስሑታን እግር ስር ተረገግጣለችና፡፡ ጩኸት ሁሉ ፍርድ ያጡ የግፉአን ድምጽ ላይሆን
እንደሚችል መጋቢት 27/0034 ዓ/ም የነበረው የኢየሩሳሌም ችሎት ነገረን፡፡ ጠማማ መሪ ካለ መንጋውም ጠማማ የመሆን እድል እንዳለው
የሚያሳይ ውሎ ነበር፡፡ ጩኸት ለተገፉት ኃይል እንደሚሆነው ሁሉ ገፊዎችም በተገፉት ቦታ ሆነው ተጨማሪ ግፍ ለመሥራት የተዛባ ፍርድ የሚያስፈርዱበት የጭካኔ
መንገዳቸው ነው፡፡
የቀረበው የክስ ፍሬ ነገር ቢወሰድ ምን ክስ መሆን የማይገባው ቢሆንም ለከሳሾቹ ደስታ ሲባል ተከሳሹን ‘ገርፎ’ ከማሰናበት
የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ሆኖም ፍጹም ከእውነት በራቀ ሁኔታ የሞት ፍርድ ተፈረደ፡፡ ዳኛው ከአለበለዚያ…ማስፈራሪያ የተነሳ ችሎቱን
በእውነትና በእውቀት መምራት እንዲሳነው ሆኗልና፡፡ “እነርሱ ግን
ይሰቀል እያሉ ጩከት አበዙ” እንዲል መጽሐፍ፡፡1 ስንት የሚያበሳጭ ጩኸት እና ጩኸታም አሁንም ቤተ ክርስቲያንንና
ዐለምን እያመሰ እንዳለ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡ የጥፋት ዐላማ እንጂ የሰውነት ሕሊና የሌለው ጩኸታም ፍርድ ሲያዛባ፣ እውነትን ስለያዘ
ሳይሆን ስለጮኸ እና ስላስጮኸ ተሰሚነት ሲያገኝ የአንዳንዱ እውነተኛ ጩኸት ደግሞ ዝናብ እንደሌለው ጉም ተንኖ ሲቀር ዐለም አሳየችን፡፡
ሞትን ያህል ውሳኔ እንዴት በአንድ ቀን፤ ከአንድ ቀንም አንሶ እንዴት በሦስት ሰዐት ችሎት?! ሰዉ አልወለደምን፣ አልዘመደምን፣
ግፍ መሥራቱን ነግ በእኔ አይልምን ያስብላል፡፡ ሕሙምን ጠይቆ፣ ሐዘንተኛን አጽናንቶ፣ ደግ ነገር ሠርቶ እንደሚመለስ ሰው ምነው
የጌታን ፍርድ ይሁን ይሁን ብለው አስቸኮሉት! ገዳይነት እንዴት እንዲህ ያስቸኩላል የሳምንት፣የወር፣ የዐመት ቀጠሮ እና ክርክር
የለምን?
‘ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው ያልረዘመው’ ትለኝ ይሆናል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አይሁድ የጌታን ልብሶች በመቅደድ መካፈላቸውን፣ እጀጠባቡን ግን ሳይቀድዱ ዕጣ መጣጣላቸው በሁለቱም ማለትም
በመቅደድና ባለመቅደድ ትንቢት መፈጸማቸውን ከደካማነታቸው/ስንፍናቸው የተነሳ ነው2 እንዳለው ምን ቀኒቱ እርሱ
ባወቀ የማታልፍ ብትሆንም እነርሱ ግን ተገድደው የገቡበት ነው ማለት አይደለም፡፡ በትንቢት ሁለት ነገር አለ፤ አስገዳጅነትና እውቀት፡፡
አስገዳጅነት የዚያ ነገር መፈጸም የማይቀር ሲያደርገው ሲሆን እውቀት ደግሞ ፍጹም አዋቂ በመሆኑ መጪውን ቀድሞ መናገሩና ማናገሩ
ነው፡፡
በአንድ ትንቢት ውስጥ አስገዳጅነትና እውቀት አንድ ላይ ሲኖሩበት እንደ የዐለም መጨረሻ ቀናት የመሰለ ይሆንና ድርጊቱ
በሰዉ ልጅ ብርታትና ጥንካሬ የማይለወጥ ሲሆን ያለው እድል በእነዚያ ቀናት ጸንቶ መገኘት ይሆናል፡፡ እውቀት ብቻ በአንድ ትንቢት
ሲኖር ደግሞ ያ ድርጊት እንዲሆን ፈጣሪ ያስገደደው ሳይሆን በሰው ልጅ በራሱ የመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ፍጹም አዋቂ በመሆኑ ግን
ይህንንም አስቀድሞ ያስነግራል፡፡
በትንቢቱ ውስጥ አስገዳጅነት ሲኖር ሰው ተገድዶ ኃጢአትን ሠራ ሳይሆን በፈተናው እንዲያልፍ ተደርጎ ፈተናውን ሳያልፍ
ቀረ የሚል መረዳትን ይሰጠናል፡፡ በትንቢት ሁል ጊዜ አስገዳጅነት አለ ማለት ግን አይደለም፤ እንደየ ትንቢቱ ይለያያልና፡፡ አዋቂነት
ግን በሁሉም ትንቢት አለ፡፡ ይህም ቅድመ አዋቂነት ሲሆን አይሁድ በፍርድ አደባባይ ተገኝተው በጩኸት ያገኙትን የተዛባ ፍርድ አስቀድሞ
እግዚአብሔር ያውቃልና በነቢዩ ቀድሞ ተናገረባቸው፡፡3
‘ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን፣ ስቀለው’ ሲሉ ትንቢት እየፈጸሙ ነበር የሚለው አገላለጽ ትክክል ቢሆንም ትንቢቱ
ይፈጸም ዘንድ ተገድደው እንዳደረጉት መቁጠር ግን ከላይ ያለውን የትንቢትን ምንነት ያላገናዘበ፣ እግዚእብሔርን ፍርድ የማያውቅ የሚያደርግ
እና ከባሕርየ እግዚአብሔር ጋር የማይሄድ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከበደል በኋላ የንስሐ መንገድ አልተዘጋባቸውም፡፡
በሐሰት መወንጀላቸው ሳያንስ በሐሰት የይሰቀልን ፍርድ ለማስፈረድ ያልተገባ ጫና መፍጠራቸው ከሰውነት ተርታ የመውጣትና
ሕሊና የማጣት መቅሰፍት ውስጥ ነበሩ ያስብላል፡፡ ስንቱ ሃይማኖተኛ ነኝ እያለ በአንድ ሰውነት ሁለት ማንነት ይዞ እየኖረ ይሆን?
በእንዲህ ዐይነቱ ዐይን ያወጣ ሸፍጥ እና ከሰውነት ማነስ ሱፍ ለብሶ በመታየቱ፣ ተከታይ በማግኘቱ ጥበበኛ የሆነ የሚመስለው ስንቱ
ይሆን? እንዲህ ዐይነቱ ሰው ቤቱን ዘግቶ፣ መስኮቱን ከፍቶ ራሱን ይጠይቅ፣ ይመርምር፣ ይናቅም፡፡ ዛሬ ዛሬ ዘረኝነትና ክርስትና
የሚስማሙና አብረው የሚሄዱ ይመስል በዘረኝነቱም በክርስትናውም እኩል አለሁበት የሚሉ ሰዎችን ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ሰው ጩኸት
ሲያሰክረው የእብድ አዋቂ ወደ መሆን ይሸጋገራል፡፡
ጲላጦስ የእውነት ታጋይ ነበር፤ እስከነጥፋቱም ቢሆን እውነትን ለማውጣት ተፋልሟል፡፡ ጩኸት ግን አሸነፈው፡፡ ስንቱ
የሚጮኸ አፍና መስኮት ስላለው እውነት ያለው እያስመሰለ አይደለምን? የሰሌዳ ቁልፍ(ኪይ ቦርድ) መንካት ስለቻለ የጻፈው ሁሉ እውነትን
የያዘ፣ በአመክንዮም የሰመረለት የሚመስለው ምስኪን እና አሳፋሪ ጸሐፊ አለ አይደለምን? ትልቅ ማስተዋልና ጥንቃቄ የሚሻውን ጉዳይ በቅዠቱ እንደታየው አውርዶ ያረክሰዋል፡፡
በተለይ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን መስደብ እንደ ዜግነት መብት የተፈቀደለት አድርጎ የሚያስብ ያለ እስኪመስል ሁለመናውን የሚከፍትባት ብዙ
ነው፡፡ ገና አንድ ጥቅስ ሲያነብብ፣ ገና አንድ አመክንዮ የታየው ሲመስለው ሳያሰላስል እኩለ ቀንም ሆነ እኩለ ሌሊት ተነስቶ ይፖስታል፡፡
እነዚህን ናቃቸው፤ የእውነት ናቃቸው፡፡ ከአንቅልፋቸው በደንብ እስኪነቁ፣ ቤታቸውን ዘግተው ራሳቸውን እስኪያዩ፣ የሚያስነውርባቸውንም
እስኪለዩ ድረስ፤ መናቃቸውን፣ ከሰውነት ተርታ መውረዳቸውን፣ በደንብ፣ በአግባቡ ንገራቸው፡፡ ከመስኮቱ አባርራቸው፤ ተቀጥረውም ከሆነ
የሚቆርሱት እንጀራ እንደማያጠግባቸው ንገራቸው የነፍስ ረሀብን ያመጣባቸዋልና፡፡
ሰውን ሳር የሚያስበሉ፣ ላባቸውን መድኃኒት ብለው የሚሸጡ፣ በሰው ሆድና ጀርባ ሰርከስ የሚሰሩ፣ ታሞ ወደ እነርሱ የሚሄደውን
‘እግዚአብሔር ይማርህ’ በማለት የሚያገኙትን በረከት ያህል እንኳ ሳያገኙበት በካራቴ ትእይንት ሰውንና ሃይማኖትን እጅግ የሚያሳንሱ፣ በወጣቱ
‘ምን ትምህርት ላይ ችክ አስባለኝ፣ እንደርሱ ካራቲስት ልሁን እንጂ’ የሚል የሞተ ጀግንነት እንዲፈጠርበት የሚያደርጉ፣ በሰው የሕመምና
መከራ ሕይወት የሚያተርፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ የዲያብሎስ የቅርብ ሰዎች የሆኑት በእውነት ያሳዝናሉ፣ ያሳፍራሉም፡፡ አጋንንትን
ከርቀት ወደ ግዝፈት ለውጦ የሚያሳይ ቁሳዊ መሳሪያ ቢኖር ከሚወርሷቸው አጋንንት በቀር ሰዎቹን እንኳ ማየት የሚሳን ይመስለኛል፡፡
አእምሮ አለኝ፣ ለጌታ ቅርብ ነኝ ከሚሉት ከእነዚህ ይልቅ ‘አእምሮአቸው ተጎድቷል፣ ይታከሙ’ ተብለው አማኑኤል ሆስፒታል የገቡት
ወገኖቻችን አስተማሪነት አላቸው፣ ነገረ እግዚአብሔርን እናይባቸዋለንና፡፡
ተከታዮቹስ፣ ከመካከላቸው ልባም የለም እንዴ፣ ሁለመናቸውን ‘ቢዝነስ’ን አለቦታው ለከተቱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች መስጠቱን
አያፍሩበትምን? መንግሥትስ ‘አንተ ከፈቀድክ ብትጠፋም ጥፋ’ ነው እንዴ? በእምነታቸው ስም የሚነገድባቸው አብያተ እምነትስ? የሃይማኖቶች
ጉባኤስ? ቢያንስ በራሳችሁ ጉዳይ ዳር የሚደርስ ሥራ ልትሠሩ ይገባል፡፡
በሁለት ወንበዴ መሀል ጌታን መስቀላቸው አንድም የወንጀል ደረጃው ከፍ ያለ ነው ለማስባል አንድም በኋላ ጌታ የተሰቀለበት
መስቀል የቱ እንደሆነ መለየት እንዳይቻል ለማድረግ ነበር እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ማብራሪያ፡፡ ነገር ግን ጲላጦስ በጌታችን
ራስጌ ላይ እንዲጻፍ ያደረገው የክሱ ጽሕፈት ይህን አስቀርቶባቸዋል፤ ሁለቱ ወንበዴዎች ከመስቀላቸው ላይ ጽሕፈት ሳይኖራቸው በጌታችን
መስቀል ላይ ግን ጽሕፈት እንዲኖር አድርጓልና፡፡ አስቀድሞ “ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ” ብሎ የጌታ መሰቀል አግባብ እንዳልሆነ
እጁን በመታጠብ የገለጸው ገዢው “ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሦሙ ለአይሁድ ውእቱ ዝንቱ-ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው”4
የሚለው የክሱ ጽሑፍ መጻፉ ስቅላቱን ከጌታቸው ወደ ራሳቸው ወደ አይሁድ የሚያሻግር ታላቅ ውሳኔ ነበር፡፡
እርሱ የአይሁድ ንጉሥ ከሆነ ንጉሣቸውን በመስቀላቸው ከሕዝብ ተርታነት የሚወርዱት እና በገዛ ተግባራቸው ራሳቸውን የሰቀሉ
ራሳቸው አይሁድ ሁነዋልና፡፡ እንደዚያ ረብ የለሽ(ሎቱ ስብሐት) አድርገው በጲላጦስ ፊት ጌታችንን እንዳላጣጣሉ አሁን ወደ ራሳቸው
ሲዞር ተንጫጩ፡፡ አካላዊ መሰቀሉ ባይደርስባቸውም የሕሊና ስቅላቱ ግን የቀረላቸው አይመስልም፡፡ አንድም ተጠይፈውታልና እርሱ ራሱን
የአይሁድ ንጉሥ እንዳለ እንጂ ንጉሣቸው እንዳልሆነ ቢነግሩትም ቆራጡ ጲላጦስ ግን ከዚያ በኋላ የሚቀመስ አልሆነም፤ “ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ
-የጻፍኩትን ጻፍኩ”፣ እረፉ፣ የሚቀየር ነገር የለም አላቸው፡፡ አብሯቸው
በአካለ ሥጋ እያለ ጌታችንን ትምህርቱና ምሥጢሩ ገብቷቸው ወደው ንጉሣችን ብለው መቀበል ባይፈልጉም በመስቀል ላይ ተሰቅሎና ሞቶ
በሥጋ ሲለያቸው ግን በክሱ ጽሕፈት ሳይወዱ ንጉሣችን እንዲሉ አደረጋቸው፡፡
ነገን ወደ መረዳት ያደጉ መሪዎች ካሉ ሁሉን ነገር የጩኸት ኃይል እያዩ ብቻ ሳይሆን ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ በማለት ጭምር
ሊፈቱ ይገባል፡፡ ይህ ድንቅ መረዳት እና ድፍረት የሚጠይቅ እንጂ አምባገነንነት አይደለምና፡፡ ከንባቡ አልፎ ምሥጢሩን ወደ መረዳት
ሲታደግ፣ ሥጋና ደም ከሚገልጠው ይልቅ የሰማይ አባት ወደሚገልጠው እውነት መድረስ ሲቻል የሚመጣ ብቃት ነው፡፡5
አይሁድ እውቅና ሰጡትም አልሰጡትም እውነታው ጌታችን የአይሁድ ንጉሥ፣ አይሁድ አባቶቻችን የሚሏቸው የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ
አምላክ መሆኑ ነውና፡፡
ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ ብለው በዙሪያቸው ያሉትን ሌቦችን፣ መናፍቃንን፣ ሴረኛ ፖለቲከኞችን ወግድ ለማለት የሚነሱ ዛሬ ቢገኙ
በይሰቀል ፍርዱ ባይሆንም በጽሕፈቱ ጲላጦስን ስለሚያስመስላቸው መልካም በሆነ፡፡ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ‘በእኔ
ላይ ከአምላኬ ሌላ ማንም ሥልጣን የለውም’ ብለው ለእስከ አሁኑ ጥፋትም ሆነ ዝምታ የደፈሩትን ያህል ለጥፋታቸው ተናዝዘው በቀረቻቸው
ዕድሜ እና ዕድል ከዘርና ፖለቲካ፣ ምንፍቅና እና ሙስና ቢርቁ የቤተ ክርስቲያን ትንሳኤ ምንኛ በተፋጠነ፡፡ ወጣቶች እኛ በብሔራችን ምክንያት/ሰበብ ከሚፈጠረው ልዩነት እና ጥላቻ ይልቅ በሃይማኖታችን
ያለን አንድነት ይበልጣል ብለው የመተባበር እንቅስቃሴ ቢጀምሩ ለምን ለሚለው ዘረኛ ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ ማለታቸው ነውና ጲላጦስን በመሰሉ፡፡
ጉልበት አለኝና መሮኛል ባዩ ሁሉ በእሳት መሀል እንኳ ዘርና ሃይማኖት ሳትለይ መጠለያ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን
ማገዶ ሲያደርጋት ተው የሚል፣ ወደ ኋላ የማይመለስ፣ ቆራጥ ጤናማ በሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት በመታደግም ሆነ ከተጠቃች
በኋላ እስከ ጥግ ድረስ በመሄድ ፍርድን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ በአጥቢያ ደረጃም ቢሆን ከታች ወደ ላይ እየተጠና እና እየተሠራ ቢሄድ
መልካም ይሆናል፡፡
ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ ማለት ለውይይት፣ ለክርክር እና ለመግባባት በርን የሚዘጋ አካሄድ ማለት ሳይሆን በውይይት፣ በክርክር፣
በንግግር አልግባባ የሚል ሲኖር በራስ ትክክለኛ አቋም መጽናትን የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ጲላጦስ ተረድቶ የሚጽፍ፣ ለጻፈውም ጽሕፈት
ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ ብሎ ለዐላማው የሚዋደቅ፣ በዚህም አምሳያነት፣ ለሚያደርገው ጤናማ ተግባር ሁሉ ጽናትን የሚላበስ እውነተኛ ክርስቲያን
ለመሆን ያብቃን፡፡
1 ማቴ. 27፣23
2 Saint
Chrysostom: Homilies on the Gospel of St. John, Homily 85: John 19: 16-18
3 መዝ. 35፣11
4 ዮሐ. 19፣19
5 ማቴ. 16፣17
No comments:
Post a Comment