ክፍል
አንድ
አሁንስ በዛ እዚያም እዚህም መናፍቃን መናፍቃን ነው፤ ዝም ብላችሁ የራሳችንን ትምህርት ለምን አታስተምሩንም፡፡ እነርሱን ማንቋሸሽ ምን ይፈይዳል ወይስ የእኛ ትክክለኛነት በእነርሱ መሳሳት የሚለካ ነውን? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች እና ስሞታዎች በቅንነት ቢሉ በተንኮል አልፎ አልፎ ይደመጣሉ፡፡ በቅንነት ከዚህ፣ በተንኮል ከዚያ፡፡ ለትምህርቱ
“ራይትና ኤክስ” የሚሰጡት የመናፍቃንን ስም ባለመጥቀስና በመጥቀስ መለኪያነት ነው፡፡
ውሎ አድሮ እንዲህ ዓይነት ሰዎች መናፍቃንን በደፈናው የተገፉ፣ ፍርድ የተጓደለባቸው፣ ሰሚ ያጡ የሚያሳዛኑ ተበዳዮች አድርገው እስከ መሳልና እግዚአብሔርን ረግመው ዲያብሎስን እስከመመረቅ የሚንደረደሩ ናቸው፡፡ የአመክንዮአቸው ጣሪያ የሙግታቸው ጫፍ በመናፍቃን ስም መጠራትና አለመጠራት የሚመዘን ነው፡፡
ጌታችን ስለ ሕይወት ሲያስተምር ሞትን፣ ስለ ብርሃን ሲያስተምር ጨለማን፣ ስለ እውነት ሲያስተምር ሐሰትን፣ ስለ መዳን ሲያስተምር ኩነኔን፣ በቀኝ ስለ መቆምን ሲያስተምር በግራ ስለ መቆምን፣ ስለ ገበሬ ሲያስተምር ጸራዊን፣ ስለ እውነተኛ መምህራን ሲያስተምር ሐሰተኛ መምህራንን፣ ስለ
መልካም እረኛ ሲያስተምር ስለ ምንደኛ እረኛን…መጥቀሱ ምን ሊባል ይችላል?
ስለ እነ እገሌ የመናገር ሱስ ወይ ካለ እነርሱ ስም መጠራት፣ ትምህርታቸውን ካለ ማውገዝ ጉባኤ አይደምቅም በሚል አልያም ከልካይ የለምና ስማቸውን እናጥፋ በሚል ሳይሆን እውነተኛ ማንነታቸውን መግለጥ፣ የትምህርታቸውን ስህተት ማሳየት የእኛ ትምህርት ከእነርሱ የተለየ እንጂ አንድ እንዳልሆነ ለማስረዳት አንዱ በመሆኑ ነው፡፡
ደግሞስ ያልሆነውን እና ያልተባለውን ከንጹሑ ዘር ጋር እየቀላቀሉ በየሚዲያው እንዲህና እንዲያ
መንጋውን ሲያወዛውዙት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ፣ ለሰው ዘር የማይገዳት ትሆን ዘንድ መጠበቅ በእግዚአብሔር ቃል መሰረት አግባብ ነውን?
አይደለም አደባባይ ወጥተው፣ አፋቸውን አስፍተው፣ መላሳቸውን አርዝመው… የሚናደፉትንና በስውር እውነትን ለመቅበር ሐሰትን ለማክበር
የሚደክሙትን የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ዐላማ ካልሆነ የማን ሊሆን ኖሯል? ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገስ
እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ ታግሰህማል ስለ ስሜም ብለህ
ጸንተህ አልደከምህም፡፡ ራዕ.2፣2
ልባቸው ከዚህ የሆኑት ከላይ በተገለጸው በቅንነት ነገር ግን በአመክንዮአቸው ድክመት ይህን ሊሉ ቢችሉም በልባቸው እና/ወይም በእግራቸው ከዚያ የሆኑት ግን ዲያብሎስ መሆኔ ለምን ተገለጸብኝ በሚል አልያም ዲያብሎስ ብሆንም ‘የነጻነት ታጋይ’ ነኝ በሚል ሽፋን ለማግኘት የሚጓዙት መንገድ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
እናም ትናንትና ተጽፏል፤ ዛሬ ለምን ይጻፋል? ወደ ፊትስ ለምን ይደጋገማል? ሳንል እንጽፋለን፣ እናስተምራለን፤
አናነባለን፣ እንማራለን፤ እግዚአብሔር በሚያሳድርብን ልብ ማለትም መንፈሳዊ ሐሴት እያደረግን ከማስተዋል ወደ ማስተዋል እናድጋለን
እንጂ ተደጋገመ በሚል ደካማ አመክንዮ ብቻ እና የጠላት ሴራ መንፈሳዊ መሳሪያችንን የምንተው ልንሆን አይጠበቅም፡፡
ለመረዳት ይጠቅም ዘንድ አቀራረቡን ከመቀያየር በቀር ቃሉ እውነት በመሆኑ ይቀያየር ወይ ይተው ዘንድ መች የሚገባው ሆነና! ለዛሬ
በየጊዜው ስልት እየቀየሩ የቅዱሳንን ምልጃ ከሚቃወሙበት አመክንዮአቸው ሁለቱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡
አንድ
በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን የሚለው ክርስቲያን የሆኑት ሁሉ መጠሪያ ብቻ ነው ስለ ማለታቸው
መናፍቃን አዲስ ኪዳን በተለየ ሁኔታ ሰዎችን ለይቶ ቅዱሳን ብሎ አይጠራም ነገር ግን ክርስቲያን የሆኑትን
በሙሉ ቅዱሳን እያለ ይጠራል በማለት ከሰው ወገን ተለይተው ቅዱሳን የሚባሉ እንደሌሉ ክርስቲያን ብሎ በሚጠራበት ፋንታ ቅዱስ
ብሎ እንደሚጠራ ያስተምራሉ፡፡
በእነርሱ አስተሳሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከክርስቲያን ሰዎችን ለይታ ቅዱሳን ማለቷ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን አስቀድሞ ስለ መኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ባልሰጠበት ሁኔታ
ደግሞ ቅዱሳን
ያማልዳሉ የሚለው ትርጉም የለሽ እንደሆነ ያትታሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ የገለጸውን በመጥቀስ ሁላችንም ጻድቃን፣ ቅዱሳን ነን ተለይቶ ቅዱስ
የተባለ የለም ለማለታቸው ምስክር ያደርጓቸዋል፡፡ ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም
መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.6፣11
ሐዋርያት በመልእክታት ሲጽፉ ቅዱሳን የሚለውን አገላለጽ በክርስትናው
ውስጥ ለተለዩ አካላት ሳይሆን ለተጠመቁ እና ወደ ክርስትናው ለመጡ በሙሉ ያለ ልዩነት ተጠቅመውበታል፡፡ ምክንያቱም ከዓለም ስለ
ተለዩ፣ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ስለተመረጡ፣ በክርስቶስ ደም ስለታጠቡ፣ ኃጢአታቸው ሁሉ ተሰርዮላቸው ፍጹም ቅዱሳን ስለሆኑ፡፡
ሐዋርያት መልእክታቸውን “ለቅዱሳን” በማለት በሮም በቆሮንቶስ እና በኤፌሶን ላሉ ክርስቲያን በሙሉ ልከዋል ይላሉ፡፡
በርግጥ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ተብለው የተጠሩት ሁሉም ክርስቲያን
በመሆናቸው ብቻ ነውን? በእምነታቸው ጽናት፣ በግብራቸው ስምረት ቅዱሳን
ተብለው የተጠሩ የሉምን? ብሎ መጠየቁ ከላይ የተገለጸውን የመናፍቃንን አመክንዮ ለመመዘን ያስችላል፡፡
ቅዱሳን የሚለው ቃል አገባብ በአዲስ ኪዳን
1ኛ ቆሮ. 1፣2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ
ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤ 2ኛ ቆሮ.1፣1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ
ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ኤፌ. 1፣ 1 በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤
ከላይ
የተጠቀሱት መናፍቃን በደፈናው ሐዋርያት መልእክት ሲጽፉ ክርስቲያን ለማለት ቅዱሳን የሚለውን
ቃል ተጠቅመዋል ለማለት እንደማስረጃነት የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡ ጥቅሶቹ በሙሉ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት የተወሰዱ ሲሆኑ አንዳቸውም
ግን ለሁሉም ክርስቲያን መጠሪያነት ስለ መቀመጣቸው አስረግጠው የሚናገሩ አይደሉም፡፡
በመጀመሪያው
ቆሮንቶስ መልእክት ላይ ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት በማለት
ለቅድስና መጠራታቸውን፣ መመረጣቸውን፣ መቅረባቸውን ከሚያሳይ በቀር በጅምላ ቅዱሳን ብሎ ሁሉንም መጥራቱን አያሳይም፡፡ በኤፌሶን
መልእክቱ ደግሞ በአንድ በኩል ቅዱሳን እና ምእመናን ብሎ መለየቱን በዚህም ከምእመናን
ውስጥ ተለይተው (ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ብልጫ ኖሯቸው) ቅዱሳን የሚባሉ እንዳሉ ሲያመለክት በሌላ ወገን ደግሞ ምእመናን ያላቸውን
በክርስቶስ
ኢየሱስም ላሉት ምእመናን በማለቱ አኗኗራቸው የሰመረ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር እንደሚገባቸው መኖር
የቻሉትን የሚያሳይ አገላለጽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህም
በራሱ በአንድ በኩል ከክርስቲያን ውስጥ ቅዱሳኑን ለይቶ ከመጥራቱ ሌላ ክርስቲያኑን ቅዱሳን ለመባል ይበቁ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን
በማለት
መስፈርቱን ይነግራቸዋል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ምእመናን አኗኗር እንዴት ነው ብንል መጽሐፍ ቅዱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደኋላ
የማያይ፣ ዐለምን የካደ፣ ጌታ አምላኩን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱም በፍጹም አሳቡም የወደደ፣…እያለ ይነግረናል፡፡
በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን የሚለው የሁለተኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ ጠቅሶ ቅዱሳን
ስለ ማለቱ ምስክር የሚሆን ሀሳብ የለውም፡፡ በአንጻሩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትርጓሜው ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱሳን የሚልን
ቃል በመጠቀሙ ያደፈ/ኃጢአት
የሰራ ሰው ቢኖር ከሰላምታው ሱታፌ እንደሌለው የሚያመለክት ነው ብሏል፡፡
በሌላም ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም
መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ጸድቃችኋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.6፣11 በሚለው አገላለጹ ከፍ ብሎ በጠቀሳቸው ልዩ ልዩ የኃጢአት ተግባራት ተሳታፊ የነበሩት፣ ከዚህም
የተነሳ ርኩሳን የሆኑት በጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምነው በመጠመቃቸው በደላቸው እንደቀረላቸው፣
ንጹሃን እንደሆኑ የሚያስረዳ ነው፡፡
ይህ ማለት ግን ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል የተባሉትን ያህል ከዚያ በኋላ በሚሰሩት
ኃጢአት አድፋችኋል፣
ረክሳችኋል፣ ተኮንናችኋል መባላቸውን የሚያስቀር አይደለም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ደግማችሁ በባርነት ቀንበር አትያዙ
የሚል እና ተመሳሳይ መልእክት ያላቸው ንባቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
በስፋት ሰፍረዋል፡፡ ገላ.5፣1
ከላይ የሰፈሩ ጥቅሶች ቅዱሳን ብሎ ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ የሚገልጽ ስለ ሆነ ቅዱሳን የሉም የሚለውን አገላለጽ የሚደግፉ ባይሆኑም ክርስቲያን
የሆኑትን በሙሉ ቅዱሳን ብሎ መግለጽ ያልተገባ ነው ማለት
ሳይሆን እንዲህ ያለ አገላለጽ ሲኖር መልእክቱ በእግዚአብሔር ረድኤት፣ በእምነታቸው ጽናት፣ በምግባራቸው ቅናት/የቀና መሆን/ ተለይተው
ቅዱሳን በሆኑት ልክ ሁሉን መጥራት ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ የመጠራት ጥሪ ወይም ክርስቲያን የመሆን ዓላማ በራሱ መቀደስ ከመሆኑ
የተነሳ በዓላማው ቅድስና ተከታዮቹን ቅዱሳን ማለት እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ እንዲህ ዐይነት አጠራር ቅዱስ የሚለው ስም የእያንዳንዱን ክርስቲያን ግብር ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ የመጠራት ዐላማውን የሚያመለክት
ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ቅዱሳን የሚሉ ጥቅሶችም ለሁሉም ክርስቲያን
የተሰጡ አይደሉምና ከክርስቲያን መካከል በእምነታቸውና በምግባራቸው ቅዱሳን የሚባሉ እንዳሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፡፡
ደግሞስ ቅዱሳን
የሚለው ቃል ለሁሉም ክርስቲያን ያለ ልዩነት መጠሪያ በመሆን ተጠቅሷል
ማለት ከክርስቲያን መካከል ብልጫ ላላቸው መጠሪያነት አልተጠቀሰም ማለትን ያስከትላልን? ከላይ እንደተገለጸው ቅዱሳን ብሎ ክርስቲያን
የሆኑትን በሙሉ መጥቀስ አግባብ አይደለም እንደማያስብል ሁሉ ቅዱሳን ብሎ ከክርስቲያን መካከል በእምነታቸው ታላቅነት በምግባራቸው
ትሩፋት የተለዩትን መጠወቀስ አግባብ የማይኮንበት አመክንዮ የለም፡፡ ቲቶ1፣8፤ ራዕ.20፣6
No comments:
Post a Comment