Monday, February 26, 2018

የአመክንዮ አቅም (ክፍል ሦስት-የመጨረሻው)


የእውቀት መገለጫ
በእምነት ይገኛል
1ኛ ቆሮ. 2፣14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡ መንፈስ የሆነን ነገር በአመክንዮ ብቻ ለሚመረምረው ሰው ሞኝነት ይመስለዋል፡፡

አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂዶ ድንጋዩን ሲሳለም፣ ቅዱሳት ስዕላቱን ሲተሻሽ አምላከ ቅዱሳን ማረኝ ሲል፣ ቅዱሳንን አማልዱኝ ሲል በሥጋዊው ሰው እይታ ሞኝነት ይሆንበታል፤ በአመክንዮ ከሚገኘው እውቀት በላይ ሌላ እውነት የሌለ ስለሚመስለውና አመክንዮም ከአቅም ማነስ የተነሳ ወደዚህ እውነት ከመድረስ ስለምትከለክለው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በእምነት ለሚመረምረው ሰው ይህ የተለየና ከአመክንዮ በላይ ካለው እውነት ጋር መገናኘት እንደሆነ ይረዳዋል፡፡  እውነተኛ የሆነው እውቀት ከእምነት በኋላ የሚመጣ ነው፤  እውነተኛ እውቀት እምነትን ይፈልጋልና፡፡ እውነተኛ እምነት ያለውም ሰው እውነተኛ እውቀትን ያገኛል፡፡

በፍልስፍና እውነተኛ እውቀትን አንደርስበትም፡፡ በፈላስፎች ዘንድ እጅግ አዋቂ እንደሆነ የሚታመነው የግሪኩ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ተይዞ ለሞት በቀረበበት ጊዜ በመጨረሻው ሰዓት እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ የመሰናበቻው ሰዓት ደርሷል፤ እኛም የየራሳችንን መንገድ እንጓዛለን፤ እኔ ወደ ሞት እናንተም ደግሞ ወደ ሕይወት ከሁለቱ ግን የትኛው እንደሚሻል ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ የለም፡፡

ስለዚህ ሶቅራጥስ የሰው ልጅ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ነው የሚሻለው ወይስ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ቢቆይ የሚለውን የሰው ልጅ መርምሮ ሊደርስበት ወይ ሊያውቀው አይችልም በማለት የሰው ልጅ የማይደርስባቸው እውቀቶች እንዳሉ ተናግሮ አልፏል፡፡ በሃይማኖት ግን ይህ ጥያቄ መልስ አለው፡፡

ዮሐ. 5፣28 በመቃብር ውስጥ ያሉት ድምጹን የሚሰሙበት ጊዜ አለና በዚህ አታድንቁ እንደተባለ ስለዚህ ሙታን ይነሳሉ በማለት ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ፣ እናም ሶቅራጥስ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው ያለውን እውቀት መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ያን እውቀት በግልጽ ለይቶ ይነግረናል፡፡

 በማቴ.25፣ 35 ስለ ትንሳኤ ሙታን እና ዘልዓለማዊ ፍርድ በግልጽ ሲያስረዳ መልካም የሠሩ በክብር ትንሳኤ የሚነሱት ወደ እኔ ኑ ሲባሉ ክፉ የሠሩ በውርደት ትንሳኤ የሚነሱት ከእኔ ራቁ የሚባሉ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ስለዚህም በፍልስፍና ሳይሆን በእምነት ወደ እውነተኛው እውቀት እንደርሳለን፡፡

የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት መልስ ያገኘው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመግለጡ፡፡ በሌላ መንገድ በፍልስፍና ልናውቀው አንችልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ፣ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ፣ ከባሕርይ አባቱ ከአብ እንደሚወለድ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይበልጥና ሳያንስ እንደሚገናዘብ… ልናውቀው የምንችለው በእምነት ብቻ ነው፡፡

እውነተኛ አውቀት መሰረቱ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ በአሁኑ በዘመናችን የጌታችንን ማንነት በተመለከተ ትክክለኛውን መልስ በማግኘትና ባለማግኘት የተከፈሉ ብዙ አመለካከቶችን እናገኛለን፡፡ እውነተኛው ማንነት የሚገኘው ግን በእምነት መሰረትነት ነው፡፡ 

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 119፣66 ላይ በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ በማለት ከማወቅ ማመን መታመን እንደሚቀድም እና ለማወቅ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡ በ2ኛ ነገ.6፣17 የሶርያ ንጉስ በእስራኤል የሚመክረውን የጥፋት ሐሳብ አስቀድሞ በማወቅ ድል እንዲሆን ያደርግ የነበረውን የእግዚአብሔርን ነቢይ ኤልሳዕን ይዘው እንዲያመጡለት ሰራዊቱን በላከ ጊዜ የነቢዩ አገልጋይ የነበረው ጊያዝ ማልዶ ሲነሳ የከበበውን አስፈሪ ሰራዊት አይቶ መምህር ሆይ ልንጠፋ ነው ባለ ጊዜ ነቢዩ አቤቱ የባርያህን ዓይኖች እንዲያዩ አድርግ ብሎ ጸለየ፡፡ የጊያዝ ዐይኖች የሶርያ ንጉሥ ሰራዊቶችን አይተዋል፤ ይህ ለሁሉም የሚታይ፣ ማንም ሰው በስሜት ሕዋስ በአመክንዮ የሚደርስበት፣ ፊት ለፊት የሚታየው እውቀት ነው፡፡ ነቢዩ የጸለየው ግን አገልጋዩ በዐይኑ ከሚያየው ባሻገር ሊያየው ያልቻለው ነገር ግን ከሚያየው ሌላ  ያላየው እውነታ ስላለ ነበር፡፡

ጊያዝም ዐይኖቹ በተገለጡ ጊዜ በኤልሳዕና በጊያዝ ወገን የቆሙ አስቀድሞ ከፈራቸው የሶሪያ ንጉሥ ሰራዊቶች ይልቅ የሚበዙና የሚያስፈሩ የእሳት ሰረገላ ያላቸው ሰማያውያን ሰራዊት ከብበዋቸው አይቷል፡፡ ስለዚህ ሰው በእምነት ሲያውቅ እና ያለ እምነት ሲያውቅ ልዩነት አለው፡፡ ያለ እምነት ሲያውቅ በሰሜት ሕዋስ ሊረዳው የሚችለውን ያህል ይረዳል፤ በእምነት ሲያውቅ ደግሞ እውነታው ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፡፡ ስለዚህም እውቀት እምነትን መሰረት ያደርጋል፡፡ 

መጠን አለው
አንድ ሰው ሁሉንንም ነገር አውቆ ሊዘልቀው አይችልም፡፡ የሰው ልጅ እግዚአብሔር በረዳውና በገለጠለት መጠን እንደ እምነቱ ያውቃል፡፡ ነገር ግን እውቀትን በሙሉ በፍጹም የሚያውቅ ፍጹም የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ለእግዚአብሔር የምንተዋቸው እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ መረዳቶች፣ እውቀቶች አሉ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛ ቆሮ.13፣9 ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን እንዳለ ሁሉንንም እውቀት መርምረን አንደርስበትም፡፡ ምድር ስንት ጥቃቅን ነገሮች አሏት? የጸጉራችን ብዛት ስንት ነው? ብለን ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን እንኳ ብንጠይቅ የሰው ልጅ መልስ ማግኘት ይቸገራል፡፡ የሰው ልጅ አእምሮ የማይደርስባቸው በተደሞ በአንክሮ ሊያያቸው የሚገቡ ዕጹብ ድንቅ ሊላቸው የሚገቡ ብዙ እውቀቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከእውቀት ከፍሎ ሊያውቅ ይችላል እንጂ እውቀትን ፈጽሞ ጠንቅቆ ማወቅ አይችልም ፍጹም የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ፡፡ ሉቃ.10፣22 ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም ይላል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ማወቅ የሚቻለው በተገለጠው ልክ ነው እንጂ ጠንቅቆ ማወቅ አይቻልም፡፡

እውቀት በልክ ነው፡፡ አንድ ሰው ሁሉንም ነገር ልወቅ ብሎ ቢነሳ ሊሆንለት አይችልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በፈቀደለት ልክ ማወቅ ይገባዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በከንቱ እንድንኖር የሚያደርጉን፣ ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ፣ ምናልባትም ለድኅነታችን ፋይዳ የሌላቸው፣ ፋይዳ ቢኖራቸውም እንኳ ልንድርስባቸው የማንችላቸውን ነገሮች ለአግዚአብሔር መተው ያስፈልጋል ለእግዚአብሔር የምንተዋቸው እውቀቶች አሉና፡፡

ቅዱስ ሄሬኔዎስ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ምን ሲሠራ ነበር ? ብሎ አንዱ ቢጠይቅ መልሱ በራሱ በእግዚአብሔር እጅ ብቻ ነው ይህ በመጻሕፍት አልተገለጠምና ወደ ስህተት እንዳናመራ እንዲህ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለእግዚአብሔር መተው አለብን ይለናል፡፡

በፍልስፍናው መንገድ የእውቀትን ውሱንነት በተመለከተ ኖውሌጅ ስኬፕቲሲስዝም የሚባል አለ፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል እውነተኛን እውቀት የሰው ልጅ ሊደርስበት አይችልም የሚሉ የተለጠጠ አስተሳሰብ ሲያራምዱ በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ እውተኛ እውቀትን ሊደርስበት ይችላል ነገር ግን እርሱን ማረጋገጥ አይቻልም የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ በፍልስፍናውም ቢሆን ፍጹም እውቀት ከሰው ልጆች ጥበብ የራቀች እንደሆነ የሚጠቁም ነገር አለ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እውነተኛ እውቀት የምናገኘው/የሚገለጥ እንጂ በሰው ልጅ ምርምር የምንደርስበት እንዳልሆነ ተገልጧል፡፡

በሌላ በኩል እውቀትን ብቻ ይዞ መጓዝም በብዙ መልኩ ስህተት ውስጥ የሚጥል ሲሆን በተለይ ደግሞ በትዕቢት እንድንጣል ያደርጋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.8፣10 እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል እንዲል፡፡ ቀሌሜንጦስ ዘሮም በመልእክቱ እውቀት በአመክንዮ ሂደት  በማሳያ/ዲሞንስትሬሽን ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ የሚናገር ሰው መርሆዎች በማሳያ ማለፍ የማይችሉ መሆናቸው በመጀመሪያ ይስማ እነርሱ በኪነጥበብም ሆነ በመልካም ፍርድ የሚታወቁ አይደሉምና፡፡ ኋለኛው የሚለዋወጡ ነገሮች ማወቂያ ነውና የመጀመሪያው ግን ክልስ ሐሳባዊ ሳይሆን ተግባራዊ ብቻ ነውና፡፡ ይላል፡፡ (እምነት የሁሉም እውቀት መሰረት-ምዕ.4)

ዮስጢኖስ ሰማዕትም እንዲህ ይላል፡፡ ስለዚህ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት እና ስለራሱና ስለሌሎች ሁሉም ነገሮች ማረጋገጫ ነው፡፡ እምነትን ማረጋገጫቸው አድርገው እርሱን የሚከተሉትና የሚያውቁት በእርሱ ዕረፍትን ያገኛሉ፡፡ (በእንተ ትንሳኤ- የእውነት ራስን የማረጋገጥ ኃይል)


ስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, February 1, 2018

የአመክንዮ አቅም (ክፍል ሁለት)


እውቀት፣ እምነት፣ እውነት
በፍልስፍናው ዓለም እነዚህን ሦስት ነገሮችን የተመለከቱ ልዩ ልዩ አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ እውቀትን የነገሮች ሁሉ የበላይ አድርገው የሚያስቡ ወገኖች አሉ፤ ከዚህ የተነሳም የክርስትናን እምነት በእውቀት ብቻ ሊመሩ ሲሞክሩ ተሰነካክለው ወድቀዋል፡፡
በሌላው ጥግ ደግሞ እውቀትን የእምነት ጠላት አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አዋቂዎች የማያምኑ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ እምነትን የእውቀት ጠላት አድርገው የሚያስቡት ደግሞ አማኞች አላዊቂ እንደሆኑ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

እውነት በእውቀትና እምነት ትገለጻለች
የካምብሪጅ የፍልስፍና መዝገበ ቃላት እውቀት የተረጋገጠ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ በማለት አውቀት፣ እምነትንና አውነትን ያስተሳስራቸዋል፡፡ አምነት ማረጋገጫው ምንድነው? እንዴትስ ይረጋገጣል? በሚለው ግን በክርስትናው እምነትና በዓለማዊው ፍልስፍና መካከል ልዩነት አለ፡፡

እምነትና እውቀት ስለ እውነት የሚመሰክሩና ወደ እውነት የሚያደርሱን ናቸው፡፡ ከሰዎች ልጆች የመረዳት አቅም በላይ፣ ከስሜት ሕዋት የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነውን ይህን  እውነት በእምነትና እምነትን መሰረት ባደረገ እውቀት እንረዳዋለን፡፡
እውነት በእምነትና በእውቀት ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት ውስጥ እግዚአብሔር አብ(አባት) ከዓለም መፈጠር፣ ከዘመን መቆጠር በፊት እግዚአብሔር ወልድን(ልጅ) ያለ እናት ወልዶታል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ልደት ይባላል፡፡ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድን ስለወለደው ግን አብ ወልድን በዘመን አይቀድመውም ይህ ከዘመናት መፈጠር በፊት ነውና፡፡

ይህንን ልደት በሥጋዊ ዐይን ማን አየው; ብንል ግን ማንም አላየውም ቢያንስ ከፍጥረታት መፈጠር በፊት ስለሆነ፤ በእምነት ግን እናውቀዋለን እምነት ይህንን የመረዳት አቅም ስለሚሰጠን፡፡ የወልድ ከአብ መወለድ እምነት ነው፤ ወልድ ከአብ ተወልዷል የሚለው በራሱ እውቀት ነው፤ ራሱ የወልድ ከአብ መወለድ ደግሞ እውነት ነው፡፡ ስለዚህም የወልድ ከአብ የመወለድ እውነትእምነት እናውቀዋለን፡፡ እውነትም በእምነትና እውቀት ይገለጻል፡፡

እውነት ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልገውም
የእውነት ማረጋገጫ ራሱ እውነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንረዳው እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ ማረጋገጫ የምንለው ከሚረጋገጠው ነገር በላይ ነውና  ከእግዚአብሔር በታች የሆኑ ነገሮችን በእግዚአብሔር እናረጋግጣቸዋለን፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ  ማረጋገጫ ማግኘት ስለማይቻል ለእውነት ሌላ ማረጋገጫ የላትም፡፡ እውነት በገዛ ራሷ የቆመች ሌላ ማረጋገጫ የማትሻ ናት፡፡ በሌላ ማረጋገጫ ተመዝና የምታልፍና የምትወድቅ ሳትሆን እውነት እውነትነቷን መጠበቅና ማረጋገጥ የምትችል የገዛ ራሷ ባለስልጣን ናት፡፡ ስለዚህም ሌሎችን በእውነት እናረጋግጣለን እንጂ እውነትን በሌላ ነገር አናረጋግጥም፡፡
በሒሳብ ትምህርት ውስጥ እንደ እውነት የሚቆጠሩና ሌላውን ለማረጋገጥ የምንጠቀምባቸው አሉ፡፡ እነዚህም አግዚዮምስ እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ በግሪክ ቋንቋ አግዚዮም ማለት በራሱ የተረጋገጠ የሚል ነው፡፡ እውነትም እንዲሁ በራሷ የምትረጋገጥ እንጂ በሌላ አትረጋገጥም፡፡ 

ዮስጢኖስ ሰማዕት ስለ ትንሳኤ በጻፈው ጽሑፍ ከእውነት በላይ ኃያል የሆነና ከእውነት በላይ ሊታመን የሚገባው ነገር ስለሌለ እውነትን በሌላ አናረጋግጠውም በራሱ የተረጋገጠ ነው እንጂ፡፡ ነገር ግን የእውነትን ማረጋገጫ የሚፈልግ ሰው ነገሮች ለስሜታችን እንደሚገለጡት ሆነው ለምን ተገለጡ የሚልን ሰው ይመስላል፡፡ በአመክንዮ የሚመጡ ነገሮች መመዘኛ ስሜት ነውና ለስሜት ራሱ ግን ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ መመዘኛ የለውም፡፡ ብሏል፡፡

የእምነት መገለጫ
በራስ አመለካከት አለመደገፍ
በአመክንዮ የምንረዳቸው ነገሮች ቢኖሩም በአመክንዮ የማንረዳቸው ግን ደግሞ ያሉና እውነት የሆኑ ነገሮችም አሉ፡፡ ከስሜት ሕዋሶቻችን የመረዳት አቅም በላይ ከአመክንዮ የመግለጽ አቅም በላይ የሆኑ ናቸውና፡፡ እምነት አመክንዮ የማይደርስባቸውን ነገሮች የምትመረምርና የምታስረዳ መሳሪያ ስለሆነች እውነትን በራሳችን አስተሳሰብ ብቻ ስንገድባት በአመክንዮ ልክ እናስቀራትና ወደ እውነት ሳንደርስ እንቀራለን፡፡

ስለዚህ እምነት የራስን አመለካከትንና መረዳትን ብቻ ትክክል ነው ከማለት የተለየ የራቀ ነገርን ትፈልጋለች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እምነት ንቁና ነጻ የሆነችን ነፍስ ትፈልጋለች፣ ከሰው ልጆች የአመክንዮ ጉድለት በላይም ከፍ ከፍ ያለችን ነፍስ ትፈልጋለች ይላል፡፡ ዕብ.11 ትርጓሜ አመክንዮ የራሱ ጉድለት ያለበት ከሆነ እና እምነት ደግሞ ከአመክንዮ አቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን የምንመረምርበት መሳሪያ ከሆነ ከአመክንዮ እስራት መፈታትና ነጻ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በዕብ 2፣4 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ሲባል ይሞኛል ማለት ሳይሆን ነፍሳችን ከአመክንዮ አስተሳሰብ በላይ ካልሆነች እውነትን መረዳት አትችልም ማለት ነው፡፡

ፍላጎትንና ችሎታን ትጠይቃለች
 ችሎታን የሚጠይቅ ነገር ታላቅ ነገር እንደሆነ ግልጽ ነውና፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ የእምነት ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ብዙዎች እምነት ሞኝነት፣ ቸልተኝነት እንዲሁ ለሁሉም የሚሆን ይመስላቸዋል፡፡ እምነት በአንጻሩ ትልቅነትን፣ አስተዋይነትን ፍላጎትንና ችሎታን ይጠይቃል፡፡ ችሎታና ፍላጎት የሌለው ሰው አማኝ ሊሆን አይችልም፡፡ እምነት ሞኝነት ሳይሆን ከአመክንዮ ከፍ ያለ ችሎታን የሚጠይቅ ነው፡፡

 በዮሐ.6፣60 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ዮሐ.6፣54-56 ብሎ ስለ ቅዱስ ቁርባን ባስተማረ ጊዜ ከሚከተሉት ብዙዎቹ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው ማን ሊሰማው ይችላል ብለው ወደ ኋላ ተመለሱ፡፡

በእምነት መስማት ያለብንን በአመክንዮ ብቻ ከሰማነው ከመደመጥ አቅም በላይ ይሆንና የሚያስጨንቅ ይሆናል፤ በእምነት ማየት ያለብንን በዐይናችን ብቻ ካየነው ከዐይናችን የማየት አቅም በላይ ይሆንና የተሳሳተ ነገር አድርገን እንወስደዋለን ከእውነትም እንርቃለን፡፡

 ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ማን ሊሰማው ይችላል ብለው ብዙዎቹ ወደ ኋላ የተመለሱት ትምህርቱ የተሳሳተ ስለሆነ አይደለም አስተማሪው እውነት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ነገር ግን ተማሪዎቹ መረዳታቸው ዝቅተኛ ስለነበረ በራሳቸው አመክንዮ ብቻ ስለገመገሙት ችሎታቸው ደካማ ስለነበረ ወደዚህ ከፍ ያለና በእምነት ወደሚደረስበት ነገር ለመድረስ ሲቸገሩ እንመለከታለን፡፡

ስለዚህ እምነት አእምሮአቸውና አስተሳሰባቸው  ትንሽ የሆኑ፣ የሥራ ፈቶችና የደካሞች ሳይሆን አእምሮአቸውን ከፍ ከፍ ያደረጉ፣ ልባቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ፣ የአስተዋዮች ነው፡፡ ሰው የሚያምነው ሥራ ፈትና ተራ ነገር ስለሆነበት ሳይሆን አእምሮውን ከፍ ስላደረገ፣ አስተዋይ፣ ታታሪ ሠራተኛ ስለሆነ ነው፡፡

በአንጻሩ አስራ ሁለቱን ሐዋርያትን እናንተ ደግሞ ልትሔዱ ትወዳላችሁን ባላቸው ጊዜ በስምዖን ጴጥሮስ በኩል ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም፡፡ ብለዋል፡፡

ይህ የሚያሳየው ወደ ኋላቸው ከተመለሱት ይልቅ ሐዋርያት የተሻለ ዐይን፣ የተሻለ ጆሮ፣ የተሻለ ችሎታ እንደነበራቸው ነው፡፡ እነዚያ የሚያስጨንቅ ንግግር ማን ሊሰማው ይችላል ብለው ተስፋ ቆርጠው ሲያስቆርጡ እነዚህ ግን ወደ ማን እንሄዳለን አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ በማለት እውነትን ተረድተውታልና፡፡

የጌታችን ንግግር ለእነዚያ የሚያስጨንቅና ሊሰማ የማይችል ሲሆንባቸው ለእነዚህ የዘላለም ሕይወት ቃልና የሚገባ(ባ-ላልቶ ይነበብ) ሆኖላቸዋል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ሃይማኖት የታታሪዎች እንጂ የሰነፎች አይደለም፡፡

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።