Monday, December 31, 2018

በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው መዝ.68፣35

ክፍል ሁለት

"በአዲስ ኪዳን አልተጠቀሰም” የማለት አግባብነት
ሌላው የሚነሳው ሀሳብ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን እንደሚያማልዱ አልተጻፈም የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በአንድነት ነው እንጂ ለየብቻ በመነጣጠል አይደለም፡፡
ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነጥሎ መቀበሉ ከአዲስ ኪዳን ተስፋ እንደሚለይና ስለ አዲስ ኪዳን የተናገረውን ራሱን ብሉይ ኪዳንንም ሐሰተኛ ማድረግ እንደሆነ ሁሉ አዲስ ኪዳንን ብቻ ነጥሎ መቀበልም አዲስ ኪዳንን መሰረት የሌለው፣ ለመታመን የሚያስቸግር፣ በመሀል የተከሰተ ተንሳፋፊ ያደርገዋል፡፡
አዲስ ኪዳንን የማያመለክት፣ የማይናገር ብሉይ ኪዳን እንደሌለን ሁሉ ብሉይ ኪዳንን መነሻ የማያደርግ ለምስክርነት የማይጠራ፣ እውቅና የማይሰጥ አዲስ ኪዳንም የለንም፡፡ ያለን በአንድ መሰረት የታነጸ ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን ያዋሐደ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ተጠቅሶ ከሆነ በአዲስ ኪዳን አለመጠቀሱ አለመኖሩን እንዴት ሊያረጋግጥ ይችላል? አዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳን የሚገነዛዘቡ እንጂ ለየብቻቸው የቆሙ አይደሉም፡፡
ጌታችን በወንጌል ሕግን እና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፣ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና…እያለ ብሉይ ኪዳንን ይጠቅሳቸዋል እንጂ ለምስክርነት የማይበቁ፣ ቃላቸው የማይጠቅም አድርጎ አልጠቀሳቸውም፡፡
ይልቁን አታመንዝር ያለውን ወደ ሴት ያየ የተመኘምበውሸት አትማል ያለውን ከቶ አትማሉ…በማለት በብሉይ ኪዳን የታዘዙትን አጽንቶአቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ በብሉይ ኪዳን ምሳሌ ሆኖ ሲሰራበት የነበረውን መስዋእት በራሱ እውነተኛ መስዋእትነት ተክቶታል፡፡ ይህ ሁሉ ከፍታ እንጂ ዝቅታ፣ መስጠት እንጂ መንጠቅ አይደለም፡፡
በብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ያማልዱ ከነበረ "በአዲስ ኪዳን ምንም አልተጠቀሰምና አያማልዱም" የሚያስብል የአመክንዮ ሙግት መሰረት የለሽ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ስለ ሥጋዊ ጉዳዮች ያማልዱ ከነበረ በአዲስ ኪዳን ከሥጋዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከፍ ባሉ፣ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ያማልዳሉ እንጂ አሁን ጸጋው ሲበዛ ጭራሹንም በዘመነ ኩነኔ የነበራቸው ጸጋ ይወሰዳል ማለት ትርጉም አይኖረውም፡፡ ጸጋውን ሽተው የታገሉትን በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመረ ከፍ ያደርጋቸዋል እንጂ ዝቅ አያደርጋቸውም፣ ጸጋን ይሰጣቸዋል እንጂ አይነጥቃቸውም፡፡
ስለዚህም በብሉይ ኪዳን ያሉ የአማላጅነት ጥቅሶችን በአዲስ ኪዳን ተጠቅሰዋልን ብለን ገና ምስክርነት የምንፈልግባቸው ሳይሆን ከአዲስ ኪዳን ዓላማ አንጻር በተጋድሎአቸው ዐይነትና ብዛት፣ በሚሰጣቸው ጸጋ እና የማማለድ ስልጣን አድማስ ሰፍተው እና በዝተው የሚታዩ መሆናቸውን የምንረዳበት ነው፡፡

ሁለት
በአጸደ ነፍስ ቅዱሳን ያማልዳሉ ማለት የእግዚአብሔር ባሕርያት መገለጫዎችን ለሰዎች መስጠት ነው ስለ ማለታቸው
አንዳንዶቹ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ ያማልዳሉ ማለት ለእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫ የሆኑትን ሁሉን አዋቂነትን፣ የአጸደ ነፍስ አማላጅነት በሁሉም ቦታ መገኘትን ስለሚጠይቅ እነዚህን ገንዘብ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቅዱሳንን አማልክት ወደ ማለት ክህደት ይወስዳል ይላሉ፡፡
እነ ማን እንደሚጸልዩ ማወቅ በሃይማኖትና በምግባር ራስን ጠብቆ የአማላጅነትን ጸጋ ከመቀበል የሚበልጥ ነውን? ነቢዩ ኤልሳዕ በአሁኑ ካለው ከቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ሊወዳደር በማይቻል ሁኔታ ስለ ሶሪያ ንጉስ የጥፋት ምክክር ጥርት ያለን መረጃ ለይሁዳ ንጉስ ማድረሱ በዚያ በዘመነ ኩነኔ የተቻለ ከሆነ በዚህ በዘመነ ምሕረት ለዚያውም ነፍስ ነጻነቷን አግኝታ ከሥጋ በላይ በምትሆንበት (በአጸደ ነፍስ) በኋላም ሥጋም ከነፍስ ጋር በምትስማማበት በሰማያዊ ቤት ለኤልሳዕ ከተሰጠው እውቀት የበለጠ የማወቅ ጸጋ ለቅዱሳን(ቅዱሳን የተባሉት ሲጀመር ጸጋው የበዛላቸውን ነውና ቅዱሳን ከሆኑ ጸጋው አላቸው ማለት ሌላን ምርምር የማይሻ ስሙ ላይ ያለ ቀጥተኛ ፍቺ ነው) አይሰጣቸውም ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐላማ በተለይ እንደ ተከራካሪዎቹ የክርክር መነሻ ከአዲስ ኪዳን አስተምህሮም ሆነ መገለጥ የሚጻረር ዐለም ዘራሽ ስሁት አመክንዮ ነው፡፡
በሁሉም ቦታ መገኘት ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሆነው በአካል በሁሉም ቦታ መገኘት በሚለው አስተምህሮ ነው፡፡ የቅዱሳን ግን በአካል በሁሉም ቦታ መገኘት ሳይሆን በረድኤት፣ በመንፈስ በሁሉም ቦታ መገኘት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔርን የባሕርይ መገለጫ ለሰዎች መስጠት ሊሆን አይችልም፡፡ ታድያ ቅዱስ ጳውሎስ ገና በምድር እያለ በአካል ከእነርሱ በመለየቱ እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ ማለቱ ትርጉም ላይኖረው ነውን፡፡
አንድ ምድራዊ ንጉ ምን በአካል ባይገኝ በሚዘረጋው የአስተዳደር መዋቅር ባለው ግዛት ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለ ያህል ሁኖ በመንፈስ የሚተሳሰር አይደለምን? ይልቁን ሰማያዊ ንጉ ያከበራቸው የንጉ ልጆች ቅዱሳን  በእውነተኛ ንጉቸው ጸጋ ሰጪነት በሁሉም ቦታ በጸጋ ቢገኙ ወደ እነርሱ የሚቀርበውን የአማላጅነት ጸሎትን ጨምሮ እርሱ ባወቀ ሌላ ነገርም ይገለጽላቸዋል ቢባል ምኑ የማይታመን ይሆናል? ከዚህም ሁሉ በላይ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ ለሚሰራው አሰራር እኛ ካላወቅነው አሰራሩ አይሰራም አልያም የለም ማለት ራስን ማዋረድ፣ በአላዋቂነት መራመድ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡
በአጸደ ሥጋም ሆነ በአጸደ ነፍስ መላእክትን ጨምሮ እግዚአብሔር ለቅዱሳን የሰጠውን የማማለድን ጸጋ ዐቅሙን እና አሰራሩን ለማወቅ እንደነርሱ ቅዱስ መሆንን ይጠይቃል፡፡
ቢያንስ እኛ እየወደቅንም እየተነሳንም የቅድስናውን መንገድ እንጀምረው፣ እንመላለስበትም ያኔ እጃችንን በአፋችን ጭነን፣ በሐሴት እንባ ተውጠን ከመጠየቅ ይልቅ ማድነቅ ምግብ ሲሆነን ከጥያቄ ሊቆጠሩ በማይችሉ ደካማ አስተሳሰቦች ተይዘን እንደነበረ ይታየናል፡፡  
                      የቅዱሳን ምልጃ ይጠብቀን፡፡

Friday, December 14, 2018

በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው መዝ.68፣35


ክፍል አንድ


አሁንስ በዛ እዚያም እዚህም መናፍቃን መናፍቃን ነው፤ ዝም ብላችሁ የራሳችንን ትምህርት ለምን አታስተምሩንም፡፡ እነርሱን ማንቋሸሽ ምን ይፈይዳል ወይስ የእኛ ትክክለኛነት በእነርሱ መሳሳት የሚለካ ነውን? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች እና ስሞታዎች በቅንነት ቢሉ በተንኮል አልፎ አልፎ ይደመጣሉ፡፡ በቅንነት ከዚህ፣ በተንኮል ከዚያ፡፡  ለትምህርቱራይትና ኤክስ” የሚሰጡት የመናፍቃንን ስም ባለመጥቀስና በመጥቀስ መለኪያነት ነው፡፡
ውሎ አድሮ እንዲህ ዓይነት ሰዎች  መናፍቃንን በደፈናው የተገፉ፣ ፍርድ የተጓደለባቸው፣ ሰሚ ያጡ የሚያሳዛኑ ተበዳዮች አድርገው እስከ መሳልና እግዚአብሔርን ረግመው ዲያብሎስን እስከመመረቅ የሚንደረደሩ ናቸው፡፡ የአመክንዮአቸው ጣሪያ የሙግታቸው ጫፍ በመናፍቃን ስም መጠራትና አለመጠራት የሚመዘን ነው፡፡
ጌታችን ስለ ሕይወት ሲያስተምር ሞትን፣ ስለ ብርሃን ሲያስተምር ጨለማን፣ ስለ እውነት ሲያስተምር ሐሰትን፣ ስለ መዳን ሲያስተምር ኩነኔን፣ በቀኝ ስለ መቆምን ሲያስተምር በግራ ስለ መቆምን፣ ስለ ገበሬ ሲያስተምር ጸራዊን፣ ስለ እውነተኛ መምህራን ሲያስተምር ሐሰተኛ መምህራንን፣  ስለ መልካም እረኛ ሲያስተምር ስለ ምንደኛ እረኛንመጥቀሱ ምን ሊባል ይችላል?
ስለ እነ እገሌ የመናገር ሱስ ወይ ካለ እነርሱ ስም መጠራት፣ ትምህርታቸውን ካለ ማውገዝ ጉባኤ አይደምቅም በሚል አልያም ከልካይ የለምና ስማቸውን እናጥፋ በሚል ሳይሆን እውነተኛ ማንነታቸውን መግለጥ፣ የትምህርታቸውን ስህተት ማሳየት የእኛ ትምህርት ከእነርሱ የተለየ እንጂ አንድ እንዳልሆነ ማስረዳት አንዱ መሆኑ ነው፡፡
ደግሞስ ያልሆነውን እና ያልተባለውን ከንጹሑ ዘር ጋር እየቀላቀሉ በየሚዲያው እንዲህና እንዲያ መንጋውን ሲያወዛውዙት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ፣ ለሰው ዘር የማይገዳት ትሆን ዘንድ መጠበቅ በእግዚአብሔር ቃል መሰረት አግባብ ነውን? አይደለም አደባባይ ወጥተው፣ አፋቸውን አስፍተው፣ መላሳቸውን አርዝመው… የሚናደፉትንና በስውር እውነትን ለመቅበር ሐሰትን ለማክበር የሚደክሙትን የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ዐላማ ካልሆነ የማን ሊሆን ኖሯል? ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገስ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ ታግሰህማል ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም፡፡ ራዕ.2፣2

ልባቸው ከዚህ የሆኑት ከላይ በተገለጸው በቅንነት ነገር ግን በአመክንዮአቸው ድክመት ይህን ሊሉ ቢችሉም በልባቸው እና/ወይም በእግራቸው ከዚያ የሆኑት ግን ዲያብሎስ መሆኔ ለምን ተገለጸብኝ በሚል አልያም ዲያብሎስ ብሆንምየነጻነት ታጋይ’ ነኝ በሚል ሽፋን ለማግኘት የሚጓዙት መንገድ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
እናም ትናንትና ተጽፏል፤ ዛሬ ለምን ይጻፋል? ወደ ፊትስ ለምን ይደጋገማል? ሳንል እንጽፋለን፣ እናስተምራለን፤ አናነባለን፣ እንማራለን፤ እግዚአብሔር በሚያሳድርብን ልብ ማለትም መንፈሳዊ ሐሴት እያደረግን ከማስተዋል ወደ ማስተዋል እናድጋለን እንጂ ተደጋገመ በሚል ደካማ አመክንዮ ብቻ እና የጠላት ሴራ መንፈሳዊ መሳሪያችንን የምንተው ልንሆን አይጠበቅም፡፡ ለመረዳት ይጠቅም ዘንድ አቀራረቡን ከመቀያየር በቀር ቃሉ እውነት በመሆኑ ይቀያየር ወይ ይተው ዘንድ መች የሚገባው ሆነና! ለዛሬ በየጊዜው ስልት እየቀየሩ የቅዱሳንን ምልጃ ከሚቃወሙበት አመክንዮአቸው ሁለቱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ 

አንድ
በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን የሚለው ክርስቲያን የሆኑት ሁሉ መጠሪያ ብቻ ነው ስለ ማለታቸው
መናፍቃን አዲስ ኪዳን በተለየ ሁኔታ ሰዎችን ለይቶ ቅዱሳን ብሎ አይጠራም ነገር ግን ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ ቅዱሳን እያለ ይጠራል በማለት ከሰው ወገን ተለይተው ቅዱሳን የሚባሉ እንደሌሉ ክርስቲያን ብሎ በሚጠራበት ፋንታ ቅዱስ ብሎ እንደሚጠራ ያስተምራሉ፡፡
በእነርሱ አስተሳሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከክርስቲያን ሰዎችን ለይታ ቅዱሳን ማለቷ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን አስቀድሞ ስለ መኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ባልሰጠበት ሁኔታ ደግሞ ቅዱሳን ያማልዳሉ የሚለው ትርጉም የለሽ እንደሆነ ያትታሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ የገለጸውን በመጥቀስ ሁላችንም ጻድቃን፣ ቅዱሳን ነን ተለይቶ ቅዱስ የተባለ የለም ለማለታቸው ምስክር ያደርጓቸዋል፡፡ ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.6፣11
ሐዋርያት በመልእክታት ሲጽፉ ቅዱሳን የሚለውን አገላለጽ በክርስትናው ውስጥ ለተለዩ አካላት ሳይሆን ለተጠመቁ እና ወደ ክርስትናው ለመጡ በሙሉ ያለ ልዩነት ተጠቅመውበታል፡፡ ምክንያቱም ከዓለም ስለ ተለዩ፣ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ስለተመረጡ፣ በክርስቶስ ደም ስለታጠቡ፣ ኃጢአታቸው ሁሉ ተሰርዮላቸው ፍጹም ቅዱሳን ስለሆኑ፡፡ ሐዋርያት መልእክታቸውን “ለቅዱሳን” በማለት በሮም በቆሮንቶስ እና በኤፌሶን ላሉ ክርስቲያን በሙሉ ልከዋል ይላሉ፡፡
በርግጥ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ተብለው የተጠሩት ሁሉም ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ነውን? በእምነታቸው ጽናት፣ በግብራቸው ስምረት ቅዱሳን ተብለው የተጠሩ የሉምን? ብሎ መጠየቁ ከላይ የተገለጸውን የመናፍቃንን አመክንዮ ለመመዘን ያስችላል፡፡

ቅዱሳን የሚለው ቃል አገባብ በአዲስ ኪዳን
1ኛ ቆሮ. 1፣2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤ 2ኛ ቆሮ.1፣1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ኤፌ. 1፣ 1 በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤
ከላይ የተጠቀሱት መናፍቃን በደፈናው ሐዋርያት መልእክት ሲጽፉ ክርስቲያን ለማለት ቅዱሳን የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል ለማለት እንደማስረጃነት የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡ ጥቅሶቹ በሙሉ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት የተወሰዱ ሲሆኑ አንዳቸውም ግን ለሁሉም ክርስቲያን መጠሪያነት ስለ መቀመጣቸው አስረግጠው የሚናገሩ አይደሉም፡፡
በመጀመሪያው ቆሮንቶስ መልእክት ላይ ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት በማለት ለቅድስና መጠራታቸውን፣ መመረጣቸውን፣ መቅረባቸውን ከሚያሳይ በቀር በጅምላ ቅዱሳን ብሎ ሁሉንም መጥራቱን አያሳይም፡፡ በኤፌሶን መልእክቱ ደግሞ በአንድ በኩል ቅዱሳን እና ምእመናን ብሎ መለየቱን በዚህም ከምእመናን ውስጥ ተለይተው (ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ብልጫ ኖሯቸው) ቅዱሳን የሚባሉ እንዳሉ ሲያመለክት በሌላ ወገን ደግሞ ምእመናን ያላቸውን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን በማለቱ አኗኗራቸው የሰመረ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር እንደሚገባቸው መኖር የቻሉትን የሚያሳይ አገላለጽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህም በራሱ በአንድ በኩል ከክርስቲያን ውስጥ ቅዱሳኑን ለይቶ ከመጥራቱ ሌላ ክርስቲያኑን ቅዱሳን ለመባል ይበቁ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን በማለት መስፈርቱን ይነግራቸዋል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ምእመናን አኗኗር እንዴት ነው ብንል መጽሐፍ ቅዱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደኋላ የማያይ፣ ዐለምን የካደ፣ ጌታ አምላኩን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱም በፍጹም አሳቡም የወደደ፣…እያለ ይነግረናል፡፡
በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን የሚለው የሁለተኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ ጠቅሶ ቅዱሳን ስለ ማለቱ ምስክር የሚሆን ሀሳብ የለውም፡፡ በአንጻሩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትርጓሜው ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱሳን የሚልን ቃል በመጠቀሙ ያደፈ/ኃጢአት የሰራ ሰው ቢኖር ከሰላምታው ሱታፌ እንደሌለው የሚያመለክት ነው ብሏል፡፡
በሌላም ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ጸድቃችኋል፡፡ 1ኛ ቆሮ.6፣11 በሚለው አገላለጹ ከፍ ብሎ በጠቀሳቸው ልዩ ልዩ የኃጢአት ተግባራት ተሳታፊ የነበሩት፣ ከዚህም የተነሳ ርኩሳን የሆኑት በጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምነው በመጠመቃቸው በደላቸው እንደቀረላቸው፣ ንጹሃን እንደሆኑ የሚያስረዳ ነው፡፡
ይህ ማለት ግን ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል የተባሉትን ያህል ከዚያ በኋላ በሚሰሩት ኃጢአት አድፋችኋል፣ ረክሳችኋል፣ ተኮንናችኋል መባላቸውን የሚያስቀር አይደለም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ደግማችሁ በባርነት ቀንበር አትያዙ የሚል እና ተመሳሳይ መልእክት ያላቸው ንባቦች  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት ሰፍረዋል፡፡ ገላ.5፣1
ከላይ የሰፈሩ ጥቅሶች ቅዱሳን ብሎ ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ የሚገልጽ ስለ ሆነ ቅዱሳን የሉም የሚለውን አገላለጽ የሚደግፉ ባይሆኑም ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ ቅዱሳን ብሎ መግለጽ ያልተገባ ነው ማለት ሳይሆን እንዲህ ያለ አገላለጽ ሲኖር መልእክቱ በእግዚአብሔር ረድኤት፣ በእምነታቸው ጽናት፣ በምግባራቸው ቅናት/የቀና መሆን/ ተለይተው ቅዱሳን በሆኑት ልክ ሁሉን መጥራት ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ የመጠራት ጥሪ ወይም ክርስቲያን የመሆን ዓላማ በራሱ መቀደስ ከመሆኑ የተነሳ በዓላማው ቅድስና ተከታዮቹን ቅዱሳን ማለት እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ እንዲህ ዐይነት አጠራር ቅዱስ የሚለው ስም የእያንዳንዱን ክርስቲያን ግብር ሳይሆን ክርስቲያን ሆኖ የመጠራት ዐላማውን የሚያመለክት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ቅዱሳን የሚሉ ጥቅሶችም ለሁሉም ክርስቲያን የተሰጡ አይደሉምና ከክርስቲያን መካከል በእምነታቸውና በምግባራቸው ቅዱሳን የሚባሉ እንዳሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፡፡
ደግሞስ ቅዱሳን የሚለው ቃል ለሁሉም ክርስቲያን ያለ ልዩነት መጠሪያ በመሆን ተጠቅሷል ማለት ከክርስቲያን መካከል ብልጫ ላላቸው መጠሪያነት አልተጠቀሰም ማለትን ያስከትላልን? ከላይ እንደተገለጸው ቅዱሳን ብሎ ክርስቲያን የሆኑትን በሙሉ መጥቀስ አግባብ አይደለም እንደማያስብል ሁሉ ቅዱሳን ብሎ ከክርስቲያን መካከል በእምነታቸው ታላቅነት በምግባራቸው ትሩፋት የተለዩትን መጠወቀስ አግባብ የማይኮንበት አመክንዮ የለም፡፡ ቲቶ1፣8፤ ራዕ.20፣6

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።