Sunday, November 17, 2013

ታላላቆች ፊደላት



(ክፍል ፩ )
መምህረ ወንጌል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ ከላካቸው አሥራ አራት መልእክታት ውስጥ ወደ ገላትያ ሰዎች የላካት የመጀመሪያይቱ እንደሆነች ይታመናል፡፡የዚህች መልእክት ይዘት በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን አካትታ ከያዘቻቸው ጉዳዮች ውስጥ በምዕራፍ ስድስት ስለ በደለ ወንድም፣ ስለ ሥጋና መንፈስ ዘር የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ሀ) ስለ በደለ ወንድም
በሃይማኖት የሚመስለን አብሮን የሚኖር ሰው ወንድማችን ነው።ለክርስቲያናዊ ሕይወቱ ዕንቅፋት የሚሆንበት ክፋት ቢገኝበት የአንድ ክርስቲያን ድርሻ ምንድን ነው?
የክርስትና ዓላማ የሰውን ልጅ ለሰማያዊ ክብር ማብቃት ነው፤ስለዚህም የአንድ ክርስቲያን ድርሻ ከዚህ እውነት የሚቀዳ ይሆናል።ሰው በማናቸውም በደል እንኳ ቢገኝ ማቅናት/ወደ ቀናው መንገድ መምራት በመንፈሳዊ ሕይወት የሚጓዝ ክርስቲያን ተግባር ነው።አንድ ክርስቲያን በክርስቲያን ወንድሙ ላይ በአግባቡ ሊያገባው ይገባል።
የሰውን ጉድፍ ስለምን አያለሁ? ጉድፉ እንዲወገድ ስለምፈልግ ነውን? የወንድሜ ጥፋት ስለምን ይታየኛል? ሕይወቱ የተስተካከለ እንዲሆን ስለምሻ ነውን? ወይስ የእርሱ የበደል ብዛት የእኔ አለመበደል ማረጋገጫ ስለሚሆነኝ? ደግሞስ በደሉን የምነግረው እንዲቃና አስቤ ነውን? ወይስ በደሉን በመንገሬ እየተሳቀቀ፣ እየሸሸ አልያም ከእኔ በታች እንደሆነ አምኖበት እንዲኖር? ወይም “በቃሌ ትምህርት በሥራዬ አርአያነት የለወጥኩት ሰው ይከው “ የሚል የመመኪያ ሃውልት ለማስቆም በመፈለግ? እግዚአብሔር ረድቶን የወንድማችን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሻሻል መሰረታዊ ፍላጎት ቢኖረን እንኳ እኛ ከእርሱ በላይ መሆናችንን ነጥብ በማስቆጠር ሥጋዊ ደስታን የምንሰበስብበት ረቂቅ ስልት የመሆን ዕድል አለው።
ስለዚህ የበደለውን ወንድም ማስተካከል ፍላጎቴ ከሆነ በየውሃት መንፈስ እንዳቃናው ተነገረኝ፤የራስ ሥጋዊ ጥቅምን ለማግኘት የሚል ሌላ ስውር ሆነ ግልጽ ዓላማ የሌለበት ማቃናት እንዲሆን፣ወንድምን ከማሳቀቅ የራቀ እንዲሆን ሊጤን ይገባል።እኔም በደል የማይደርስበት፣ እንዳይደርስበትም በንጽሕናው ዋስትና ያገኘ ሰው አይደለሁምና ወንድሜን ሳቃና በቅንነትና ራስን በማየት መሆኑን መመርመር ይጠበቅብኛል።
ለ) ስለ ሥጋና መንፈስ ዘር
የሥጋ አስተሳሰብን መሰረት አድርገን የምንጓዘው መንገድ ከእግዚአብሔር ለይቶ የኃጢአት ተገዢ ወደ መሆን ያደርሰናል።የሥጋ ዘር ቢዘራ የሥጋ ፍሬ ይለቀምበታል፤የመንፈስ ዘር ቢዘራ የመንፈስ ፍሬ ይለቀምበታል። በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለፀው በሥጋ የሚዘራው የዝሙት፣ የገዳይነት፣ የምቀኝነት ፣የዘፋኝነት፣ የራስ ወዳድነት …ዘር የሞትን ፍሬ ያፈራል፤በመንፈስ የሚዘራው የፍቅር፣ የትዕግስት ፣ የበጎነት፣ ራስን የመግዛት…ዘር የሕይወትን ፍሬ ያፈራል።  ሰው በሰውነቱ የመንፈስን ዘር ዘርቶ የመንፈስን ፍሬ ያጭድ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
በሥጋ ዘር የመንፈስን ፍሬ መልቀም ከቶ እንዴት ይቻላል! ወንድሜ ሆይ የመንፈስን ፍሬ በሥጋ ዘር ታገኛት ዘንድ ምን ያህል ደከምህ! አንተ ትዘፍናለህ ነገር ግን አመስጋኝ ነኝ ትላለህ ፤ አንተ ትቀየማለህ ነገር ግን ይቅር ባይ እንደሆንክ ታስባለህ ፤አንተ ትጣላለህ ነገር ግን ፍቅርን የምታውቃት ይመስለሃል፤ አንተ ታመነዝራለህ ነገር ግን ራስህን የምታውቅ ጠንቃቃ አማኝ፣ አገልጋይ አድርገህ  ትቆጥራለህ።በሥጋ ዘር የመንፈስን ፍሬ ለመልቀም መጣጣር ምንኛ አድካሚና የማይቻል ነው! ቢሆንም አሁንም ይህንኑ እናደርገዋለን ።ይህ ተግባራችን የድንጋይን  ግንብ ለማፍረስ በእጁ እየገፋ የሚውል ምስኪን ሰውን ያስመስለን ይሆን? ግንቡ ፈጽሞ ፈቅ የማይል መሆኑን ቢያውቅም የተሻለ አማራጭ ከመፈለግ ይልቅ አሁንም እንዲሁ ያደርጋል፤ ምናልባትም እንዲህ አድርጎ አልገፋ ሲለው ለምን ብሎ ይበሳጭ ይሆናል።
የኃጢአት ግድግዳን ለመግፋት፣ የዝሙት ጾርን ለማራቅ፣ ከምቀኝነት መንፈስ ለመላቀቅ፣ ከምስጋና የለሽ ሕይወት ለመጠበቅ የመንፈስን ዘር ዝራ።የመንፈስ ዘር ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ፣ከአባቶች ጋር መተዋወቅ ፣ወደ ገዳም መሄድ ፣በመንፈሳዊ ተቋም መማር፣ የሰንበት ት/ቤት ወይ የአገልግሎት ማኅበር አባል ወይ አስተባባሪ መሆን፣ የሰበካ ጉባኤ አባል መሆን ፣ማስቀደስ ፣መቀደስ፣ መስበክ፣ መሰበክ በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ለታቦታት ምንጣፍ ማንጠፍ ብቻ እንዳይመስልህ ይህን ሁሉ በጥልቀት የሚያስብ ጥልቅ መንፈሳዊነትም ጭምር እንጂ ።
ሐዋርያው እነዚህን ሀሳቦች ሲያጠቃልል እንዲህ ይላል፤” እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደጻፍሁላችሁ እዩ”(ገላ.፮፣፲፩)፡፡ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ታላላቆች ፊደላት፤በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በታላላቆች ፊደላት የተመላ ነው፤የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ስርዓት ትውፊት አጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎቷ ምንኛ በታላላቆች ፊደላት የተዋቡ ናቸው!ለማሳያነት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጥቂቶች ታላላቆች ፊደላት እንመለከታለን፡፡
ታላላቆች ፊደላት
ጠላትነትን አደርጋለሁ (መጽሐፍ ቅዱስ)
በአጭሩ ተናገሩ (መጽሐፍ ቅዱስ)
እምነት ጨምርልን (መጽሐፍ ቅዱስ)
ቁርጥ ልመናችንን ስማን (መጽሐፈ ኪዳን)
የተጨነቀችይቱን ነፍስ ሁሉ አሳርፍ (መጽሐፈ ቅዳሴ)
ከተቀራረቡ ተራሮች መሠረት …የኃጢአቱ ክብደት የሚበልጥ …(መጽሐፈ ምስጢር)
የምጽፍባትን ብዕር ስበራት ስበራት አለኝ (አረጋዊ መንፈሳዊ)
እኔ ቸል ስል ሞት ደርሶብኛል(ውዳሴ አምላክ)
ሰጠሁ ተቀበልኩ (ዮሐንስ አፈወርቅ)
ኑ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ (ገድለ ጊዮርጊስ)

Wednesday, October 9, 2013

እምነት ምንድን ነው?(ክፍል ሀ)


           እምነት የተወሰነን ነገር ወይ  ሁሉንም ነገር ኃይል ብለው ለሚቀበሉት ለአንድ አካል ወይ ለብዙ አካላት ባለቤትነት መስጠት ነው።ስለዚህም በማመን ውስጥ የሚያምንና የሚታመን አሉ።ከዓለም ታሪክ እንደምንረዳው ሰዎች ስለ ተወሰነ ጉዳይ ወይ ስለ ሁሉም ጉዳዮች አንድን ወይ ብዙ ነገሮችን  ይከተላሉ።በአጠቃላይ በማመን ውስጥ ለአጭር ጊዜም ይሁን ለዘለዓለም፣ ለውሱን ጉዳይ ይሁን ለሁሉም ጉዳዮች ለአንድ ወይ ለብዙ አካላት ተገዢ መሆንን ያመለክታል፤ማድረግ አለማድረግ መማር መቅጣት … የሚችል/ሉ አካል/ላት እንዳለ/ሉ መቀበልን ያሳያል።
           ሰው ወንዙን፣ ተራራውን፣ ዛፉን፣ ድንጋዩን፣ እሳቱን፣ ጉልበቱን፣ አስተሳሰቡን፣የማይታይን አምላክ… ያምን ይሆናል።”እምነት አለ፤ የለም፤” ብሎ ከመከራከር ይልቅ “እምነት ስንት ነው? እውነተኛና ሐሰተኛ እምነትስ አለ ?” ብሎ መጠየቁ ይበልጥ ሚዛን ይደፋል።ምክንያቱም ሰው “በምንም አላምንም” በማለት ከእምነት ውጭ መኖር እንደሚችል ያሳየ ቢመስለውም “በምንም አላምንም” በሚለው አስተሳሰቡ ያምናል ማለት ነው።”ራሴንም እጠራጠራለሁ” ቢልም እንኳ “ራሱን በመጠራጠሩ” ያምንበታል ማለት ነው።ስለዚህ የሚያምነው ነገር እና ዓላማ ሊለያይ ይችላል እንጂ ምንም የማያምን ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው።በተለምዶ እምነት የሌላቸው (እምነት የለሽ) ሰዎች የሚባሉ ይኖሩ ይሆናል፤ይህ ማለት ከራሳቸው (አስተሳሰባቸው) በቀር የሚያመልኩት ሌላ አካል የሌላቸው መሆኑን ለመጠቆም የተቀመጠ ነው።ስለ ሁሉም ጉዳይ ዘልዓለማዊ የሆነውን የፈጠረውን እንጂ ያልተፈጠረውን አምላክ ማመን ይገባል።
አምልኮ በአንድ አምላክ

            በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች አንድ ሁሉን ቻይ ዘልዓለማዊ እና የማይታይ አምላክ እንዳለ ያምናሉ፤ነገር ግን አንድ እምነት የላቸውም፤ምክንያቱ ምንድነው?
            ምንም እንኳ በአንድ ዘልዓለማዊ  የማይታይና ሁሉን ቻይ አምላክ ማመን አንድነት ቢሆንም ያልተብራራ አንድነት እንደሆነ ደግሞ ግልጽ ነው።ስለዚህ የእምነት አንድነት በአንድ የማይታይና ሁሉን ቻይ ዘልዓለማዊ ፈራጅ ፈጣሪ…ከማመን በላይም የሚፈልገው ሌላ አንድነት አለ።ይህ አምላክ ምን ባህርያት አሉት(አንድነት ሦስትነት፣በተለየ አካል ሰው መሆን…)? የሰጣቸው ትእዛዛት ፣ለሰው ልጅ የሰጠው ተስፋ፣ ያስቀመጠው የድኅነት መንገድ፣ ስለ ዘልዓለማዊ ሕይወት ያለው ትምህርት ምንድን ናቸው?…የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።እነዚህን ጥያቄዎች ፈጽሞ ማለፍ የማይቻል በመሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች የተለያዩ መልሶች ያሏቸው ሁሉ የተለያዩ እምነቶች ሊሆኑ የግድ ነው።ስለዚህም በእምነት ፈጽሞ አንድ አይደሉም።
          ይህም ማለት ከኤስያ ተነስተው ወደ ኢትዮያ ለመምጣት የወሰኑ ሰዎች  አንዱ ወደ ካናዳ ፣ሌላው ወደ ስፔይን ፣ሌላው ደግሞ ወደ ሞሮኮ የመሄድ ያህል ይሆናል።በኢትዮያ ያሉትን ክፍላተ ሀገር ፣ወንዞችና ተራሮች ፣ሰዎች ፣ታሪኮች …(ፍጹም ራሳቸውን ሆነው) በካናዳ ወይ በስፔይን ወይም ደግሞ በሞሮኮ አገር ማግኘት ከቶ እንዴት ይቻላቸዋል? ስለዚህም እነዚህ ሰዎች ኢትዮያን ጎበኘናት፤ እናውቃታለን፤ ብለው ቢናገሩ ስተው ከማሳት በቀር ሌላ ምን ይፈይዳሉ!
         በመሆኑም ሁሉም እምነቶች ሊያድኑ አይችሉም ፤ የሚያድን አንድ ትክክለኛ እምነት ብቻ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።ሰዎችም የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉት “ማዳን ከሚችሉት ከተለያዩ እምነቶች አንዱን ልከተል” በሚል ሳይሆን “ብቸኛ የድኅነት መንገድ የሆነውን እምነት ልከተል” በሚል መሆኑ የታወቀ ነው፤ስለዚህ በየእምነቱ ያለ ሰው የሚያምነው እምነት ብቻ ትክክለኛ  መሆኑን መመስከሩ ሊያስነቅፈው አይችልም።ይህ ማለት ግን ሌላው የፈለገውንና አምንበታለሁ የሚልበትን  እምነት የማመን መብት የለውም ማለት አይደለም።

Sunday, September 8, 2013

የክርስቲያኖች አኗኗር




                   ክርስቲያኖች ከሌሎች ሰዎች ወይ በሀገር ወይ በቋንቋ ወይ በሚያዩዋቸው ልማዶች አይለያዩም። እነርሱ በራሳቸው ከተሞች አይኖሩምና፤ የተለየ የአነጋገር ስልት አይጠቀሙምና፤ ወጣ ባለ ነገር የሚገለጽ ሕይወትንም አይኖሩምና ፡፡ እነርሱ የሚከተሉት ሥነ ምግባር በማንኛውም ክልስ ሐሳብ ወይ ጣልቃ ገብ ሰዎች የተቀየሰ አይደለም ፤ጥቂቶች እንደሚያደርጉትም የማንኛውም የሰው ልጅ መመሪያ አስፋፊ አድርገው ራሳቸውን አያስተዋውቁም። ነገር ግን በግሪክና በባርባር ከተሞች በመኖር እያንዳንዳቸው በተወሰኑበት መሠረት ከአለባበስ ከምግብ እንዲሁም ከተቀሩት መደበኛ ሥነ ምግባሮች አንጻር የነባር ነዋሪዎችን ልማዶች በመከተል የራሳቸውን አስደናቂና ማራኪ የሆነውን የሕይወት ዘይቤ ይገልጡልናል፡፡
                   እነርሱ በራሳቸው ከተሞች ይኖራሉ ነገር ግን እንደ ተራ መጻተኞች ሆነው ፡፡ እንደ ዜጎች በሁሉም ነገሮች ከሌሎች ጋር ይጋራሉ ቢሆንም እንደ ባዕድ ይቸገራሉ፡፡ማንኛውም ባዕድ መሬት ለእነርሱ እንደ እናት መሬት ነው እንዲሁም ማንኛውም የተወለዱበት መሬታቸው ለእነርሱ እንደ መጻተኞች መሬት ነው፡፡ሌሎች ሁሉ እንደሚያደርጉት እነርሱ ይጋባሉ ልጆችን ይወልዳሉ ዘራቸውን ግን አያጠፉም።የጋራ ጠረጴዛ/ማዕድ አላቸው የጋራ አልጋ/ርኩሰት ግን የላቸውም፡፡እነርሱ በሥጋ ውስጥ ናቸው ነገር ግን ሥጋን እየተከተሉ አይኖሩም። ቀኖቻቸውን በምድር ላይ ያሳልፋሉ ነገር ግን እነርሱ የመንግስተ ሰማያት ዜጎች ናቸው፡፡
                 የተሰጡትን ሕግጋት ይከተላሉ በተመሳሳይ ጊዜም በሕይወታቸው አብልጠው ይከተሏቸዋል፡፡ሁሉንም ሰዎች ይወዳሉ እንዲሁም በሁሉም ይተቻሉ፡፡እነርሱ ያልታወቁና የተወቀሱ ናቸው፤ እነርሱ ለሞት የተሰጡ ናቸው እንዲሁም ለሕይወት የተጠበቁ ናቸው፡፡እነርሱ ድሆች ናቸው ቢሆንም ብዙዎችን ባለጠጎች ያደርጋሉ፤ እነርሱ ሁሉን ያጡ ናቸው ቢሆንም ሁሉም የሞላላቸው ናቸው፤እነርሱ የተዋረዱ ናቸው ቢሆንም አብዝተው በተዋረዱ መጠን የተከበሩ ናቸው፡፡እነርሱ መጥፎ ይነገርባቸዋል ቢሆንም የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡እነርሱ የተጠሉና የተባረኩ ናቸው፡፡እነርሱ የተሰደቡና ስድቡን በበጎ የሚመልሱ ናቸው፤እነርሱ ጥሩ ያደርጋሉ ቢሆንም እንደ ክፉ ሰሪ ይቀጣሉ።በተቀጡ ጊዜ ወደ ሕይወት እንደሚፈጥን ሰው ደስ ይላቸዋል፤እነርሱ እንደ ባዕድ በአይሁድ የተጠቁ ናቸው በግሪኮችም የተገፉ ናቸው ቢሆንም እነርሱን የሚጠሉ ለጥላቻቸው ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም፡፡
የማቴተስ መልዕክት ወደ ዲዮግናጠስ  /2ኛ መቶ ዓመት

Tuesday, July 16, 2013

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።