እኛ እንኳ በኖርንባቸው ጊዜያት ሁሉ ጥቃቅን የጊዜ መለኪያዎች እየተደመሩ
ሰከንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት፣ ዕለት፣ ሰሙን፣ ወርሕ፣ ዓመት፣ ዘመን ሲሆኑ ይኸው አየን፡፡ የእነዚህ ጊዜያት መምጣትና መሄድ እኛንም
ጨምሮ በተፈጥሮ ላይ የሚገለጡ ምልክቶችን እየተወ ወቅቶችን ያበጃል፡፡ የመሬቱ መርጠብ፣ የአበቦች መፍካት፣ የሳሮችና ቅጠሎች መለምለም፣
የአዝርእት መብቀልና ማፍራት፣ ደግሞም መጠውለግ፣ መድረቅና መጥፋት ከሰው ልጅ መጸነስ፣ መወለድና ማደግ እንዲሁም መሸምገልና ማለፍ
ጋር እየተሰናሰሉ በፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ሰሌዳነት መዓልትና ሌሊት እንዲሁም ብርሃንና ጨለማ ብዙ ሲናገሩ ይኖራሉ፡፡
እነርሱ ታሪክን፣ ሕይወትንና ሞትን ተሸከሙ፣ የደስተኛውን ፍስሐ፣ የለቀስተኛውን
ሐዘን ተመለከቱ፡፡ እንስሳቱ ብቻ ሳይሆኑ ተራሮችና ሸንተረሮች፣ ከፍታውና ዝቅታው በሙሉ በዘመን ዋዕይና ቁር፣ ነፋስና ዝናብ፣ ብርሃንና
ጨለማ ‘ሰውነታቸው’ ሲለዋወጥ ራሳቸው የዘመን ተራኪ እስከ መሆን በቁ፡፡ የሰው ልጅም ተፈጥሮን ተመልክቶ ወቅቱን ይለያል፡፡ በዘመን
ውስጥ ያለውን የምስጢር ቋጠሮ ማን ሊፈታ ይችላል? ማንስ ያስተውለዋል? ራሱ ዘመንስ ስለ ማን የሚናገር ነው?
በመዝሙር 74 ቁጥር 16-17 ላይ እንደሰፈረው “ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው አንተ ፀሐዩንና ጨረቃዉን አዘጋጀህ፡፡
አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ” የሚያስብል ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ይህንን የምስጢር ቋጠሮ
እንዴት እንደገለጸው እስኪ እንመልከት፡፡ መዝ.104፣ 2-23፡፡ እንዲህ ከተረከ በኋላም ቁጥር 24 ላይ “አቤቱ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው ሁሉን በጥበብ አደረግህ ምድርም ከፍጥረትህ
ተሞላች” ይላል፡፡
የዚሁ ልበ አምላክና ነቢይ ቅዱስ ዳዊት ‘ሁሉን በጥበብ አደረግህ’ የሚለው የመንፈስ እይታ አንዱ ማሳያ ሆኗት
ቅድስት ቤተክርስቲያን የምስጋና አዝማናትን አሰናድታ በዘመናት ሁሉ በጥበብ እግዚአብሔርን ታመሰግንበታለች፡፡ ቅዱስ ዳዊት “በሕይወቴ ሳለሁ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ
እዘምራለሁ” ያስባለው ይህ ነውና፡፡መዝ.104:33
በቅድስት ቤተክርስቲያን የምስጋና ሥርዓት አንዱ ዓመት ክረምት፣ መፀው፣
ሐጋይ እና ፀደይ በሚሉ እያንዳንዳቸው ዘጠና ቀናትን በያዙ ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ወቅት ቀናትም በዘመን ተከፋፍሎ
ለምስጋና የተሰናዳ ነው፡፡ ይህ ያለንበት ወቅት ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25 ባለው ውስጥ ነውና ፀደይ እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም
ዘመነ ዘርእ/የዘር ዘመን/ ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት በራሱ ዘመነ ትንሳኤ፣ ዘመነ ዕርገት፣ ዘመነ ጰራቅሊጦስና ዘመነ አስተምህሮ
በሚባሉ አራት አዝማናት የተከፋፈለ
ዘርና ወንጌል
ፀደይ በተሰኘው በዚህ ዘመን ደጋግሞ የታረሰውና ዘር ለመቀበል ዝግጁ የሆነው
መሬት ይዘራበታል፡፡ ገበሬው በዓመት ለሚያገኘው ምርት ዝግጅት የሚያደርገው ገና ከበሬዎቹ ምርጫ፣ ከሞፈሩ፣ ድግሩና ቀንበሩ ልዝብነት፣
ከማረሻው ስለት ጀምሮ ነው፡፡ ለሞፈርነት፣ ለድግርነት እንዲሁም አንዱንም ሆነ ሁለቱን በሬዎችን አስተባብሮ በአንድነት ለአንድ ስራ
እንዲሰማሩ ለሚያደርገው ለቀንበርነት የሚሆን እንጨት በባለሙያ ታይቶ ይመረጣል አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጎበት በክብር ይቀመጣል፡፡
ገና ሳይዘራ፣ ሳይበቅልበትና፣ ሳያሸት/ለእሸትነት ሳይበቃ/ ገበሬው በእርሻው ወቅት መሬቱን እየገመሰ ሲያርስ ተስፋው ይታየዋል የድንጋይ
የጭንጫ አልያም የለም መሬት መሆን እና አለመሆን በማረሻው እየወጋ መሬቱን ይመረምረዋል፡፡ ለዚህም ብቁ የሆነ ማረሻ ከባለሙያው
ዘንድ ሄዶ ያሰራል፡፡
የሚዘራው ዘር እንክርዳድ ያልተቀላቀለበት፣ ነቀዝ ያልበላው ንጹሕ ዘር
መሆን አለበት፡፡ አልያማ ትጋቱ ከንቱ ሁኖ ክብሩም ወርዶ ካልደከመው ገበሬ ጋር ተካክሎ ማሳው የእንክርዳድ ይሆንበታል፡፡ ለዚህም
ሲል የዓመት ዘር ለይቶ በጥንቃቄና በክብር ከአይጥና ነቀዝ ብቻ ሳይሆን ከቀለብነትም ጠብቆ ያቆየዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት አልፎ
የተዘራው ዘር እንደ ተቀበለው መሬት የሚያፈራም የማያፈራም ይሆናል፡፡ ያልተዘራ እና ያልተፈለገ እንክርዳድም ሊበቅል ይችላል፡፡
የአረሙ ጥበቃው መከሩ እና ክምችቱ ሂደት መዘርዘር ጊዜውና ቦታው ይገድባል፡፡ በእውነትም የገበሬ ተግባር/ግብርና ‘ማፍራት’ የሚባል
ትልቅ ተልእኮ ያለውና በብዙ በተቀናጁ እና ተከታታይነት ባላቸው ትእግስት በሚፈልጉ ተግባራት የተሞላ ነው፡፡
ከላይ በጥቂቱ የተገለጸውን የግብርና ሂደት በማንሳት ወንጌልን በዘር መስሎ
ስለ ሰባኪው፣ ስለ ስብከቱ ስለ ተሰባኪው፣ ስለ ወንጌል ፍሬው የሕይወት መምህር እውነተኛ ገበሬ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በማቴዎስ ወንጌል ም.13 ላይ እንዴት እንዳስተማረ ስንመለከት እንደነቃለን፡፡ ይህ ወቅት ይህንን ክቡር ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
ከቅዳሴዋ ጀምሮ በልዩ ልዩ የምስጋና ሥርዐቷ የምታመሰጥርበት ወቅት ነው- ዘመነ ፀደይ፡፡
እንክርዳድ
ከዚህ ጽሑፍ ዓላማ አንጻር ከላይ የተገለጸውን የጌታችንን ትምህርት ወደ
ማብራራት ባይገባም ስለ እንክርዳድ ካስተማረው ውስጥ ጥቂት ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ እንክርዳድ በስንዴ ማሳ ላይ ገበሬው ሳይፈልገው
በቅሎ የሚገኝ አረም ነው፡፡ እንክርዳድ እንኳን ሰው እንስሳትም ቢመገቡት ይገድላቸዋልና በገበሬው ተፈልጎ የሚዘራ አይደለም፡፡ እንክርዳድን
ፈልገው የሚዘሩትም ፀራዊ/ጠላት በሚለው መለያ ጌታችን የጠራቸው
የዲያብሎስ የግብር ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ዓለማችን በተለይ በዘመናችን እንክርዳድ ሲበቅልባት ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ እንዲያውም
ስንዴን ከሚዘሩ ገበሬዎችና ስንዴን ከሚያበቅሉ ማሳዎች ይልቅ እንክርዳድን የሚዘሩ ገበሬዎችና እንክርዳድን የሚያበቅሉ ማሳዎች ሳይበዙ
አይቀሩም፡፡ በአዲስ ኪዳን ስለ እንክርዳድ ብዙ መባሉም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡”/ማቴ.7፣15/
“ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ፡፡”/ማር.13፣22/
ሲል ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት
ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው
የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፡፡”/2ኛ ጴጥ.2፣1/ “ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ
ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ወደ ዓለም ወጥተዋልና፡፡”/1ኛ ዮሐ.4፣1/
ብለዋል፡፡
እንክርዳድ እድገቱ ከስንዴ ጋር ተመሳስሎ ነውና ልባሙ ገበሬ ካልሆነ በቀር
ሁሉም አይለየውም፡፡ እንደማይፈለግ ስለሚያውቅም ተለይቶ እንዳይነቀል እና እንዳይቃጠል ራሱን ከስንዴ ጋር ማመሳሰሉ የሚጠበቅ ነው፡፡
የእንክርዳድ ክፋቱ እንክርዳድ ከመሆኑ በላይ ተቀላቅሎ መብቀሉ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ለብቻው ብቻ የሚበቅል ቢሆን ኖሮማ የሚፈልጉት
ዲያብሎስና ልጆቹ ብቻ ባሳደጉት ነበር፤ የብርሃን ልጆችም ስንዴውን ብቻ ባፈሩ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በሌሊት ሰዎች ሲተኙ ጠላት
የሚዘራው መሆኑ የገበሬው ትጋት ምን ያህል መሆን እንዳለበት ያመላክታል፡፡
“ብዙዎች ለክርስቶስ
መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ፡፡ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው
አምላክ ነው ክብራቸው በነውራቸው ነው አሳባቸው ምድራዊ ነው፡፡”/ፊል.3፣18-19/ በማለት ሐዋርያው እንዳሳሰበው ሐሳባቸው ምድራዊ ስለሆነ እንክርዳድ የሚዘሩበትም መንገድ ፍጹም ምድራዊ እስከመሆን የሚደርስ
ነው፡፡ እንክርዳዳቸውን በልዩ ልዩ መንገድ የሚዘሩ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ላይ በአንዱ መሰረታዊ በሆነው የስህተት መንገዳቸው ላይ
ትኩረት ተደርጓል፡፡
ትርጓሜ
የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጓሜ በተመለከተ ትርጓሜ/ተርጓሚ ያስፈልጋል ወይስ
አያስፈልግም? ከሚለው ጀምሮ ትክክለኛ የትርጉም ሂደት የቱ ነው? እንዲሁም የመተርጎም መብት የማን ነው? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎችን
ከግምት ባለማስገባት እና ልቅ በሆነ መንገድ በመሄድ በየጊዜው እርሻ በሆነው በሰው ልጅ ልብ ላይ የሚዘራው እንክርዳድ ብዛት እና
እግዚአብሔርን የመዳፈር ጥግ መጠን የለውም፡፡
የትርጓሜ እና ተርጓሚ አስፈላጊነት
አንዳንዶቹ በኤፌ.3፣4 ላይ ያለውን “ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን
ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፡፡” የሚለውን እና መሰል ጥቅሶችን በመጥቀስ ‘አንድ ሰው በራሱ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መረዳት ይችላል ትርጉምና ተርጓሚ
አያስፈልገውም’ ይላሉ፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው በራሱ አንብቦ ተረዳ ማለት ምን ማለት ነው? ለሚያነበው ነገር ትርጓሜ ባለመስጠት
መረዳት የሚባል ነገር በራሱ እንዴት ሊኖር ይችላል? አንዱን መጽሐፍ ቅዱስን ያነበቡ አሥር ሰዎችስ በመሰረታዊ ሐሳባቸው የተለያዩ አሥር አረዳዶችን መያዛቸው ትክክል ሊሆን ይችላልን?
በመሰረቱ አንድ መጽሐፍ የተጻፉበት ፊደላትና ቃላት ስርዓተ ነጥቡን ጨምሮ እንዲያስተላልፉ የሚፈለገው ፊደላቱና ቃላቱ የተሸከሙትን
ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህም በተመሳሳይ ፊደላትና ቃላት ፍጹም ግንኙነት የሌላቸው፣ በዓላማም ጭምር የተለያዩ ሐሳቦችን ሰዎች የሚይዙ
ከሆነ ወይ ሰዎቹ መጽሐፉን አልተረዱትም ወይ መጽሐፉ እዚያም እዚህም
የሚቀባጥር የማይረባ ነው፡፡
ጌታችን ሐዋርያትን “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ብሎ ማዘዙ ሐዋርያት “እንጀራ ባንይዝ ነው “ በሚል በምድራዊ አንጀራ/ስንቅ መያዝና አለመያዝ
ተርጉመው/ተረድተው እርስ በርስ ሲነጋገሩ ትርጓሜያቸው/አረዳዳቸው ስህተት መሆኑን ከዚህ ቀደም ጥቂቱን አበርክቶ ብዙውን እንደመገበ
አለማስተዋላቸውን በመጥቀስ ስለ ምድራዊ እንጀራ አለመናገሩን ይልቁን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ከተባለው ከሐሰት ትምህርት
እንዲጠበቁ መሆኑን አብራርቶላቸዋል፡፡ ማቴ.16፣6-12 ከላይ በኤፌሶን የተጠቀሰውም ሆነ በ2ኛ ቆሮ.1፣13-14 የተጻፈው “ከምታነቡትና ከምታስተውሉት ሌላ አንጽፍላችሁምና” ማለቱ ለመረዳት
የሰው ልጅ የማንበብ ወይም የመስማት ድርሻ እንዳለው ገለጸ እንጂ ‘በማንበብ
ብቻ ወደ መረዳት ትደርሳላችሁ’ የሚል አይደለም፡፡ በ2ኛ ቆሮ. ላይም ‘ሌላ እንግዳ ትምህርት አዲስ ሥጋዊ ጥበብን አናመጣባችሁም’ ማለቱ እንጂ እያንዳንዱ ስላነበበ ብቻ ይረዳል ማለት
አይደለም፡፡
በርግጥ ሳይተረጉሙ ያነበቡትን መረዳት የሚባል ነገር ስለሌለ
አንብቦ/ተርጉሞ/ ይረዳ ይሆናል፤ ግን የትኛውን መረዳት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲተላለፍ የፈለገውን ሐሳብ ወይስ
ሌላ? ለምሳሌ ሉተርና ወገኖቹ ‘እያንዳንዱ በራሱ አንብቦ መጽሐፍ ቅዱስን
መረዳት ይችላል’ አሉ፤ እነርሱ በራሳቸው አነበቡ የተለያየ አረዳድም ያዙ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እነርሱ የተረዷቸው የተለያዩ
ሐሳቦች ናቸው ማለት ነውን? እንዲህ መሆኑስ ትርጉም ይሰጣልን? ይኸው እኔ አንብቤ እነርሱ ከሚሉት ሐሳብ ያልሆነ ሌላ ሐሳብ ገባኝ
በእነርሱ እይታ እኔ የገባኝ ከእነርሱ ተቃራኒ የሆነው ሐሳብ ትክክል ነውን? ትክክል ካልሆነስ እኔን ማስረዳት የሚችሉት ሲተረጉሙልኝ
አይደለምን?(ይህም ትርጉም አስፈላጊ እንደሆነ ይመሰክርባቸዋል) ከዚህም ብሶባቸው ‘ምንም ተቃራኒ ሐሳብ ብንይዝ አንተም እኛም ትክክል ነን’ ካሉ ደግሞ ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተላልፈው የራሱ ሐሳብ የለውም፤ ከንቱ ነው’ ብለው እያፌዙ እንደሆነ ይረዱት፡፡
የሕይወት መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ ያለውና ሰዎችን ወደ ሕይወት የሚመራ እውነተኛ ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡
እንዲህ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡት መሰረታዊ የሐሳብ ልዩነት የሚገጥማቸው ከሆነ የተረዱበት መንገድ ስሕተት ነው ማለት
ነው፡፡ ስሕተቱ የሚታረምበት፣ ትክክለኛ አረዳድ እንዲኖረን የሚያደርገው ትርጓሜ ሲሆን ትርጓሜውን የሚሰጠን እውነተኛ ተርጓሚም ያስፈልጋል፡፡
በ2ኛ ጴጥ.3፣16 ላይ እንደሰፈረው “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚቸግር
ነገር አለ፡፡… ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ፡፡” ሲል ‘እነዚህን’ ብሎ ቅዱሳት መጻሕፍት ማለት የፈለጉትን ሐሳብ ትተው ሌላ
ሐሳብ እንደሚሉ አድርገው/አጣምመው እንደሚተረጉሙ ያሳያል፡፡ የተጣመመ ትርጉም መኖርም በአንጻሩ ያልተጣመመ ትርጉም ለመኖር አስረጂ
ነው፡፡
ፊልጶስ ትንቢተ ኢሳይያስን ሲያነብ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ‘የምታነበውን ታስተውለዋለህን?’ በማለት የጠየቀው ማንበባችን ለማስተዋል ለመረዳት መንገድ ሊሆን እንደሚገባ የሚያሳይ
ነው፡፡ ፊልጶስ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል” ለሚለው
የጃንደረባው ጥያቄ አዘል መልስ ተቃውሞ ሳይሆን ይሁንታ በማሳየት ከእርሱ ጋር በሰረገላው ላይ በመቀመጥ ጃንደረባው ከያዘው መጽሐፍ
ጀምሮ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ ሐዋ.8፣30-35 ይህም ትርጓሜና ተረጓሚ መኖሩ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ መሆኑንም ጭምር ያሳያል፡፡
ትውፊት-የትክክለኛ ትርጓሜ ሂደት
የቅዱሳት መጻሕፍትን ሐሳብ በትክክል ለመረዳት ትርጓሜ አስፈላጊ እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ የትክክለኛ ትርጓሜ ምንነት
አለማወቅ ‘ትርጓሜ አያስፈልግም’ ከሚሉት ባልተናነሰ ጥፋት የሚያደርስ
ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንትና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተለያዩ አረዳድ እና እምነት አላቸው፡፡ ሁሉም
ግን/ፕሮቴስታንቶች በተግባር የሚያደርጉትን መተርጎምን ወደ ጎን በማለት ትርጓሜን ባይቀበሉም/ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፤ እውነት
አንዲት ናትና፡፡ ለምሳሌ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ
ፍጹም እግዚአብሔርም ፍጹም ሰውም ነው የሚለው የተዋሕዶ ትምህርት ክርስቶስ አንድ አካል ሁለት ባሕርያት የሆነ ፍጹም እግዚአብሔርና ፍጹም ሰው ነው ከሚለው ፈጽሞ የተለየን ማንነት
የሚገልጽ እምነት ነው፡፡ ስለዚህም ትክክለኛ ትርጓሜ የቱ ነው የሚለው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡
‘እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ፤
እንዲህ ብዬ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ ተቀበረም መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ… ‘1ኛ ቆሮ.15፣3-4 የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ምስክርነት እርሱ የተቀበለውን አሳልፎ እንደሰጠ ያስረዳል፡፡ ይህ የተቀበሉትን
የመስጠት ሂደት በግእዝ ትውፊት ይባላል፤ ቅብብሎሽ የሚል የአማርኛ ፍቺ አለው፡፡ ዘወትር በቅዳሴያችን ወንጌል
ሊነበብ ሲል ታላቅ የሚባለው ካህን በዕለቱ ወንጌል ለሚያነብበው ካህን
አመቻችቶ ይይዝለት ዘንድ ለዲያቆኑ ሲሰጠው ዘአወፈየኒ አቡየ ካህን
አወፍየከ እሁየ ዲያቆን-አባቴ ካህን ያቀበለኝን(ወንጌልን) ወንድሜ ዲያቆን አቀብለሃለሁ/አስረክብሃለሁ ማለቱ ከላይ የተቀበለውን
ቅብብሎሽ ማስጠበቁ ነው፡፡
ትውፊት መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የተጻፈውም ያለተጻፈውም በአጠቃላይ ክርስቶስ የመሰረታት የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን
ሕያው መንፈስ የሚተላለፍበት የቅብብሎሽ ቦይ ነው፡፡ ሐዋርያት አስቀድመው አልጻፉም አስቀድመው ግን በትውፊቱ ነበሩ፡፡ ጌታችን ሲያስተምር፣
አሳስተው የተረዱትን ሲተረጉም፣ ምግብ ሲያበረክት ብቻ ሳይሆን እንዴት እንዳበረከተ፤ መከራ መቀበሉን ብቻ ሳይሆን እንዴት መከራ
እንደተቀበለ… መጻፍ የማይገልጣቸውን የእይታ መረዳቶችን ጭምር በሕሊናቸው የሳሉ እና የኖሩበት ናቸው፡፡
አሁን ትውፊት አያስፈልግም ባዮቹ ራሳቸው እንኳ የሚይዙትን
መጽሐፍ ቅዱስ/ማጣመማቸው እንዳለ ሆኖ/ ያስገኘላቸው ትውፊት ብቻ ነው፡፡ ትውፊት ማለት ታሪክ ማለት አይደለም፤ ትውፊት ማለት የእውነተኛይቱ
ቤተ ክርስቲያን ሁለንተና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍበት ሕያው የሆነ አሁንም የሚሰራ የቅብብሎሽ መንገድ እንጂ፡፡ በትውፊት
ውስጥ ታሪክ ይኖራል እንጂ ከታማኝነት ምንጭነትም ሆነ ቀጣይ ከመሆን ማንነት የተነሳ ታሪክ ትውፊትን አይተካም፡፡
የመተርጎም መብት የማን ነው?
“…በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም
አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፡፡” 2ኛጴጥ.1፣20-21 እንዳለው ሐዋርያው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ወይ ትንቢት ወይ የትንቢት ፍጻሜ ስለሆነ ማንም ለገዛ ራሱ ሐሳብ በሚመች
ወይ እንዲህ ተረድቼዋለሁ በሚል ትርጓሜ ሊሰጥ ከሚገባው አካል
ሌላ ትርጓሜ የሚሰጥ እንዳይኖር ያሳስባል፡፡ የመተርጎም መብት ለሁሉም የተሰጠ ሳይሆን አግባብነት ያለው አካል መብት እና ሐላፊነት
ብቻ እንደሆነም የሚያስረዳ ነው፡፡ የዚህም ባለቤት ከጌታችን መገለጥ ጀምሮ በሐዋርያት፣ በሐዋርያውያን አበውና በሊቃውንት አድርጎ
በቤተ ክርስቲያን መከፈል ጊዜም የመከፈል አደጋ ያልደረሰባቸውና እውነተኛውን ሕያው ትውፊትን የያዙት የምስራቅ አኃት አብያተ ክርስቲያናት
ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ እውነተኛውን ትውፊት ጠብቃ ስለማቆየቷ በሌሎቹ ጭምር ምስክርነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን ናት፡፡ በልዩ ልዩ ርእሶች ለሚነሱ ትምህርቶች ሆነ ሐሳቦች ትርጉም የመስጠት መብት ያላት ይህችው ቤተ ክርስቲያን በትውፊትዋ
መሰረት የያዘችውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ የሚያስረዱላት መምህራን አሏት፡፡
ነገረ እግዚአብሔርን የሚያስረዳውን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ተራ የሒሳብ ትምህርት የቁጥሮች ድምር ማንም አንብቦ መረዳት ይችላል በሚል ሌላው ትርጓሜን ሊያስቀር ሆነ
እንደፈቀደ የመተርጎም መብት ሊኖረው አይችልም የመጠየቅና የመማር መብት እንጂ፡፡
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ የተለያየ አረዳድ ላይ የሚደረስ ከሆነ ትክክለኛ አረዳድ መገኘት ያለበት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል ወይ ሐሳብ በትውፊት የነበሩት ሐዋርያት፣
ሐዋርያውያን አበው፣ ሊቃውንት እንዴት ተረጎሙት፣ እንዴት ተረዱት፣ እንዴትስ ኖሩበት? በሚለው ትውፊትን በመከተል መንገድ
እንጂ ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ ነኝ ባይ የመተርጎምን
ነጻነት በመስጠት አይደለም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በትውፊት የቆየ እና ከትውፊት ውጪ የሆነ ሁለት ሰዎች ተገናኝተው ሲነጋገሩ እንኳ
ለመረዳት የሚቸግር ነገር አለ፤ በትውፊት የትርጓሜ ‘ምህዳር’ ስፋት ከማወቅና ካለማወቅ የተነሳ፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያምንና ቅዱሳንን
አድኑን ብሎ መለመን በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ኢየሱስ ክርስቶስን
አድነን ብሎ ከመለመን የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ሐሳቡ በሁለቱም
ዘንድ ማዳን የሚል ቢሆንም በመጀመሪያው ከፈጣሪያችሁ ከእግዚአብሔር ባገኛችሁት ባለሟልነት ምህረትን ለምኑልን፣ አሰጡን
ማለት ሲሆን በሁለተኛው ደግም አንተ ሁሉን የምታደርግ በቀራንዮ ተሰቅለህ…
ያዳንከን አምላክ በስልጣንህና በቸርነትህ ማረን ማለት ነው፡፡ ከትውፊት ውጪ የሆነው ሰው ግን ማዳን የሚለውን ብቻ ይዞ በመሄድ የመጀመሪያውን ሐሳብና ትምህርት
ጭራሹኑ በደፈናው ያወግዘዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ የተቀበልንበት ሕያው ትውፊት ግን ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንደማይጋጭ ብቻ ሳይሆን የሚያብራራ
መሆኑን ይመሰክርልናል፡፡ እንዲሁ መድኃኒትን ያስገኘሽልን ስንል
አምላክን በማህፀንሽ ተሸክመሽ በራሱ አስቻይነት የወለድሽው እንጂ
‘የፈጠርሽው’ ማለት እንዳልሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሐምሳ
በሐዋርያት ላይ ወረደ ስንል ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ
ማለት እንጂ ራሱ መንፈስ ቅዱስን በባሕርዩ ተሸከሙት ማለት እንዳልሆነ ከትውፊት ውጪ ለሆነ ሰው መረዳት ያዳግታል፡፡ እንዲህ
የመሰሉ አገላለጾች ብዛት ያላቸውና አማኞቹም ተረድተዋቸው በአግባቡ የሚጠቀሙባቸው ቢሆኑም ከዚህ እሳቤ ውጪ የሆኑት ግን በለመዱት
ቀመር ይህ ስህተት ነው እያሉ ከትውፊት ዳኝነት ውጭ ይዳኛሉ፡፡
ዘርአ ወንጌል-የወንጌል ዘር ያልነቀዘ፣ እንክርዳድ ያልተቀላቀለበት፣ ጽሩይ ሆኖ በፍጥረታት ልብ እንዲዘራ ከእውነተኛው
ምንጭ ተቀድቶ፣ ከትውፊት በተገኘው ትምህርትና የሕይወት አኗኗር ተተርጉሞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የማያፈራው በጭንጫ፣ በመንገድ ዳር
አልያም በእሾህ ላይ ሲወድቅ ብቻ ሳይሆን ዘሩ ንጹሕ ዘር ሳይሆን ሲቀር ጭምር እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ለዚህም መምህራነ ወንጌል
ንጹሑን ዘር እየዘሩ እንክርዳዱን ለይቶ ማሳወቅ ሲኖርባቸው እኛ ምእመናንም የእንክርዳዱን እና የንጹሑን ዘር ጠባያት ከትውፊት ባገኘነው
መረዳት እየመረመርን መልካሙን ዘር እንጂ በስመ ወንጌል እንክርዳዱን በልባችን ላለማዘራት መትጋት ይኖርብናል፡፡ ከዚህም ሌላ እንክርዳድ
የሚዘሩትንም ሆነ እንክርዳድ የተዘራባቸውን ወደ እውነተኛው የግብርና ስራ እንዲመለሱ የምንነሳበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር