መጥቀስና
ማገናዘብ
ቅዱስ መጽሐፍ የሰው ልጅ በጊዜ፣ በቦታ እና ለማስታወስ ካለው
ውሱንነት የተነሳ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በቅዱሳን በኩል የሰጠው የሕይወት መመሪያ ነው፡፡ በመጽሐፉ የሰፈረው ቃልም ቃለ እግዚአብሔር
ሲሆን ሰዎች የተጻፈውን ተረድተው ሕይወት እንዲያገኙበት ተሰጥቶአል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ያሉ ቃላተ እግዚአብሔር ዋና ድርሻም በቃልነታችው
አማካይነት የእግዚአብሔርን ሐሳብ፣ ትምህርት፣ ፍቅር፣ ትዕዛዝ…ማድረስ
ነው፡፡
ስለዚህም ቃላትን አገኘን ብለን እንደመሰለን ብንተረጉም ሕይወትን
ለማሰጠት ከተጻፉ ቃላት ሞትን ልንቀጥፍ እንችላለን፡፡ ጌታችን በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ መላእክትን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር
ልጅስ ከሆንህ ወደ ታች ራስህን ወርውር ተብሎ ነበር፡፡ ይህም ከመዝሙር
90፣11-12 የተጠቀሰ እንጂ በቅዱስ መጽሐፍ የሌለ አይደለም፡፡ ይሁንና ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጻፈ ራሱ ክርስቶስ ለዚህ መልስ
ሲሰጥ አንተ የጠቀስከው ቃል በቅዱስ መጽሐፍ የለም በሚል ሳይሆን
ጌታ
አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል፡፡ በማለት ነው ዘዳ.6፣16፡፡
በዚህም ዲያብሎስ ከቅዱስ መጽሐፍ ሲጠቅስ ጌታችንም ከአንዱ
ቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የዲያብሎስ ስሕተት የጌታችን ትክክል የሆነው ከቃሉ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ አለመገኘትና መገኘት
የተነሳ ሳይሆን ቃሉ የያዘውን ሐሳብ በአግባቡ ባለመጠቀምና በመጠቀም (ባለመረዳትና በመረዳት-ማስረዳት) የመጣ ልዩነት ነው፡፡ ማቴ.4፣5-7 በዚህም መሰረት ቅዱሳት መጻሕፍትን በዚሁ አግባብነት
እየጠቀሱ እውነቱን መረዳት ይገባል እንጂ እንደ ዲያብሎስ ጥቅስ ስለጠቀሱ ብቻ ትክክል መሆን አይቻልም፡፡ የተሐድሶ አካሄድ ዓላማቸውን
ለማሳካት ልክ እንደ ዲያብሎስ ጥቅስ አገኘሁ ብሎ መጥቀስን እንጂ ማገናዘብን፣ መረዳትን፣ ከጌታችን ጀምሮ በሐዋርያት በኩል በትውፊት
የተላለፈውን እውነተኛውን መረዳት መከተልን አይደለምና ከስሕተት ይከታል፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ተሐድሶዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የሚሉት
ስሕተትና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንመለከታለን፡፡
ተማላጅ
እንጂ አማላጅ አይደለም
ኢየሱስ የእኔ
አማላጅ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላ አማላጅ የለኝም አያስፈልገኝም ኢየሱስ በቂዬ ነው የሚሉ ፍጹም ፕሮቴስታንታዊ የሆኑ
ትምህርቶችና አገላለጾች በተሐድሶዎች ዘንድ የሚባሉ እና የሚታመኑ ናቸው፡፡ ኢየሱስ በቂዬ ነው ሲባልም በደፈናው ለሚያየው ሰው ትክክለኛ አገላለጽ ሊመስለው ይችላል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ
ክርስቲያንም ከሚያስፈልገው በላይ ጉዳዮችን የምታበዛ፣ ነገሮችን የምታካብድ፣
አማላጆችን የምትፈጥር የሚመስላቸው የዋሃንም አይታጡም፡፡
አማላጅነት አንድ አካል በራሱ ስልጣን፣ አቅም እና ማንነት
ሊያደርገው የማይችለውን ነገር ለሌላ ለሚችል አካል የሚያቀርበውና ካለው ባለሟልነት የተነሳም ተሰሚነት ያለው ልመና ነው፡፡ አማላጅነት
ልመና ነው፡፡ ለማኝነት በመሰረታዊነት ሲታይ የማድረግ አቅም ሲታጣ የማስደረግ አቅም ሲኖር የሚደረግ ነው፡፡
ቅዱሳንን አማላጅ የምንለውም በባሕርያቸው አምላክ ያልሆኑ ሁሉን በራሳቸው ስልጣን ማድረግ የማይችሉ ነገር ግን ከእውነተኛው
አምላክ ጋር ካላቸው ቀረቤታ( በፍቅሩ በመኖር፣ ሕግን በመፈጸም) የማማለድ ባለሟልነት የተሰጣቸው ስለሆኑ ነው፡፡ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። እንዲል ያዕ.5፣16 ከእግዚአብሄር ጆሮ ደርሶ የሚደመጥ መልካም ምላሽን የሚያስገኝ
ጸሎት ማናችንም የምንጸልየው ጸሎት ሳይሆን ጻድቃን በአጠቃላይ ቅዱሳን የሚጸልዩት ጸሎት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህም ሲባል እኔ ቅዱስ አይደለሁምና መጸለይ አይገባኝም የሚያስብል ሳይሆን የቅዱሳን
ምልጃ ያስፈልገኛል እግዚአብሔር ያመለከተው መንገድ ነው የሚያስብልና በዚያ እንድንጸና የሚረዳ ነው፡፡ የቅዱሳኑ የመቀደስ፣
ጻድቅ የመሆን መንገዱም ይኸው ራሱ ነውና፡፡
ፍጹም አምላክ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰውም ነውና ያለቀሰ፣ የተራበ፣
የደከመ ሲሆን፣ የሚሞት ሥጋን ተዋሕዶ ሰው መሆኑን ለማስረዳት፣ በሌላም በኩል በአዳም/በእኛ በበደልነው በሰው ልጆች ቦታ ሆኖ እኛ
የምንለምነውን ልመና፣ የምናነባውን እንባ በማቅረቡ ለመነ አማለደ
የሚሉ ቃላቶችን እናገኛለን፡፡ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። ሉቃ.22፣32
እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ
ተሰማለት፤ዕብ.5፣7 ማለቱም ለዚህ ነው፡፡
የእነዚህ ቃላት ዓላማ ግን ራሱ አምላክ ሳይሆን ቀርቶ፣ አቅም
ያጣ ሆኖ እንደሚለምን ለማመልከት አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እርሱ ሌላ ሰጪ፣ ቀዳሚ የሌለው እግዚአብሔር፣ አምላክ፣ ፈጣሪ መሆኑ ተጠቅሷልና፡፡
ሮሜ 9፣5፣ ኤፌ.2፣10 ሁል ጊዜ የምንጠቅሰው በዮሐንስ ወንጌል
ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ ላይ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። በማለት ቁጥር 14 ላይ ሥጋን መዋሐዱን
የተናገረለት ያ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በግልጽ ይመሰክራልና፡፡ ሰው በመሆኑ እግዚአብሔር መሆኑ አልቀረምና፤ ታዲያ እግዚአብሔር ጸለየ፣ አማለደ ተብሎ ቢነገር ፍቺው ምንድነው? ስለዚህ
ዋና ሐሳቡን ትቶ አማላጅ ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያስወጣናል፡፡
ተግባሩ ካለ መቻል የተነሳ ሳይሆን ከመቻል የተነሳ የማዳን
ሂደት ነውና አቅም እንዳጣ አማላጅ የሚለው ቅጽል እና ሐሳብ
አይመጥነውም፡፡ ምንም እንኳ ነገሮች ከመሆናቸው በፊት የሚያውቅ፣ ለነቢያትም ሀብተ ትንቢትን የሰጠ ቢሆንም ትንቢትን የሚናገር ከመሆኑ
የተነሳ ነቢይ ማለት ለፍጡራን የሰጠውን የነቢይነት ማዕረግ እንደሚያስመስለውና ከአምላክነት አንጻር ነቢይ ብሎ መጥራቱ ዝቅታ በመሆኑ
ነቢይ እንደማንለው ሁሉ፡፡
በሌላ በኩል እርሱ
ከአብ የሚቀበል፣ የሚያንስ አድርገው የሚያስቡ ወገኖች የሚከተሉትን
ጥቅሶች አንብቡ ቢባሉ በጥድፊያ ይዘልቋቸዋል፡፡ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። ማቴ.28፣18፣ የሰውን
ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ
በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። ዮሐ.8፣28፣ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም
ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። ዮሐ.10፣18 ተሰጠኝ፣ አባቴ እንዳስተማረኝ፣ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ፣
ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ…፡፡ እነዚህ አገላለጾች አይሁድ አብን እናውቃለን፣
እግዚአብሔር አባታችን ነው፣… ይሉ ስለነበር ከአብ አለመለየቱን፣ እንዲያውም ፈጽሞ በአብ ዘንድ ያለ መሆኑን፣ አብን እናውቃለን
ባዮች እርሱን(ወልድን) አለማወቃቸው የሚያስደንቅና ያልተገባ መሆኑን፣ አብን የማወቅ መስፈርቱ ወልድን ማወቅ፣ ወልድንም የማወቅ
መስፈርቱ አብን ማወቅ መሆኑን ለማስረዳት እንጂ እርሱ አቅም የሌለው ፣ ከሌላው የሚቀበል መሆኑን ለመግለጽ እንዳልሆነ ማስተዋል
ይገባል፡፡
ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር
አብን የሚያውቅ የለም። ማቴ.11፣27 እንዲል፡፡ ዳግመኛም እንዲህ ብሏል፡፡ እንግዲህ። አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤
እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው። ዮሐ.8፣19 እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤
እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ዮሐ.8፣42 አይሁድ አባታችን እግዚአብሔር ነው ብለው ስለተከራከሩት በተግባር የእግዚአብሔር
ልጆች ሆነው ቢሆን ኖሮ ክርስቶስን ለመግደል ሊፈልጉት ቀርቶ ሊወድዱት ይገባ ስለነበር እርሱ ከአብ ዘንድ አይደለም በሚል እርሱን ላለመቀበል ምክንያት እንዳይሆናቸው ከራሴ አልመጣሁም፣ ያ አባታችን የምትሉት ላከኝ በሚሉ አገላለጾች
ሁሉን ለአብ ሰጥቶ ተናግሯቸዋል፡፡ ይህም ማለት ወልድ ከአብ የተለየ ፈቃድ እንደሌለው፣ በፈቃድ አንድ እንደሆኑ፣ የፈቃድ አንድነታቸውንም
ከራሴ አልመጣሁም አብ ላከኝ በማለት የአብ ተቃራኒ እና አብን
የማያውቅ፣ አብ የማያውቀውና በራሱ ፍላጎት ብቻ የተገለጸ አድርገው ማሰባቸው ስሕተት እንደሆነ ሲያሳይ ነው፡፡
እንዲህማ ባይሆን
ኖሮ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ እንደተገለጸው በገዛ ስልጣኑ ሕግን እንዴት ይሰራ ነበር? ራሱን ከአብ ጋር በስልጣን
አንድ አድርጎ እኔና አብ አንድ ነን፣ እኔን ያየ አብን አየ…እንዴት
ይላቸው ነበር? ዮሐ.10፣30፤ ዮሐ.14፣6-12፡፡ የኋላ ኋላ
አይሁድ ሊገድሉት የፈለጉትስ ራሱን እግዚአብሔር አድርጓል በሚል
አልነበረምን? ኢየሱስ፦ ከአባቴ
ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን
ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። እንዲል ዮሐ. 10፣32-33
ከላይ እንደተመለከተው
አንድ ካህን(ቄስ) በትህትና በዲያቆን ቦታ ሆኖ ቢቀድስ እርሱ ዲቁና
እንጂ ቅስና የለውም ማለት ሞኝነት እንደሆነ ሁሉ ከማዳኑ ስራው ተነስቶ ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ማለት የተሳሳተ የማንነት
ትምህርት ነው፡፡
ከትንሳኤ በኋላም
ቢሆን ጌታችን ተፈጸመ ኩሉ ብሎ ከእንግዲህ በኃይል ለፍርድ እንጂ
በትህትና እንደማይገለጽ ነግሮናል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ።…ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ
አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። ዮሐ.19፣28-30፤ ማቴ.26፣64 እነዚህ ወገኖች ስለ እነርሱም ሊያምልድ ዘወትር በሕይወት
ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ዕብ.7፣25 የሚለውን ገጸ ንባብ
ጠቅሰው ከትንሳኤ በኋላም አማላጅ ነው ለማለት ይደፍራሉ፡፡ የጥቅሱ
ሐሳብ ግን ክርስቶስ ያቀረበው የቀራንዮ ቤዛነት አንድ ጊዜ የተፈጸመ ለዘላለም የሚሰራ መሆኑን ለማመልከት እንጂ እነርሱ እንደሚሉትስ
አይደለም፡፡ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት
በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።
ዕብ.7፣27 ስለሚልባቸው፡፡
በእኛ ተገብቶ ያቀረበው ልመናውም ቢሆን ከትንሳኤው በፊት የፈጸመው
ነው እንጂ አሁን የሚያደርገው አይደለም፡፡ አሁንማ በቀኝ ተቀምጧል በግርማ ለፍርድ ይመጣል፤ ታድያ አሁን ላይስ ቢሆን እንዴት አማላጅ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ ማር.16፣19፤ ራዕ.1፣7
አምላክ
ሆኖ አማላጅ መሆን ትርጉም አለውን?
ቅዱሳት መጻሕፍት ለኑፋቄአቸው መንገድ ሲያሳጧቸው አንዳንዶቹ የሚሉት ደግሞ አምላክም አማላጅም ነው የሚል ነው፡፡ አምላክነቱ
እንዳለ ሁኖ አማላጅ ነው እያልን ነው ቢሉ እንኳ በአንድ በኩል አምላክነትና አማላጅነት የሚቃረኑና አብረው የማይሄዱ ሲሆን(አምላክ
ከሆነ ማንን፣ እንደምን ይለምናል? አማላጅስ ከሆነ እንዴት ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ባሕርይ እንዳለው አምላክ ይባላል?) በሌላ
በኩል ደግሞ በእውነት እንደዚህ የሚሉ ቢሆኑ ስለ አምላክነቱ መቼ ሰበኩ? እርሱንስ በፍጡር የሚደረገውን ተግባር እንደሚሰራ ቆጥረው
አማላጅ የማይሉት ቢሆን ኖሮ እንዴት የቅዱሳንን አማላጅነት አስቀሩ?
የቅዱሳንን ተግባር ለእርሱ ሰጥተው አማላጅ ስለሚሉት አይደለምን!
አምላክነትን ያላስቀማ አማላጅነት ነው ያለው ካሉን ደግሞ ይህስ አስታራቂነት፣ መሐሪነት የሚለው አገላለጽ ይስማማዋል እንላለን፡፡
ማስታረቁም ከራሱ፣ ከአባቱ ከአብ፣ ከሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ኑ እንዋቀስ ብሎ ሲለምነን በመሰረታዊነት ለማኝ የሚል ማንነት ሳይሆን መሐሪ፣ ይቅር ባይ፣
አዳኝ የሚለው ማንነት ይገልጸዋል፡፡ ልመናው የማድረግ ስልጣን፣ ባሕርይ ከማጣት ሳይሆን ካለው መሐሪነት ስለመሆኑ የሚያስረዳ
ነውና፡፡ ኢሳ.1፣18 ደግሞም እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች
ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። በሚለው እግዚአብሔር…እንደሚማልድ ብሎ እኛን አንደሚለምነን ያሳያል፤ ነገር
ግን ሐሳቡን እንጂ ቃሉን ብቻ አንመለከትምና አእምሮ እንዳጣ ሰው
ሆነን እግዚአብሔርን ለማኝ፣ አማላጅ የምንለው ሳይሆን እንደባለ
አእምሮ ሰው ሆነን ምሕረቱ የበዛ፣ መሐሪ፣ አዳኝ እንለዋል፡፡
ወልደ
እግዚአብሔር ሕያው
እንግዲህ ይህንን ታላቅ የማንነት ጥያቄ ከአይሁድ ባሻገር ራሱ
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠይቆ ትክክለኛውን መልስም ነግሮናል፡፡ በፊልጶስ ቂሣርያ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ሐዋርያትን በጠየቀ ጊዜ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ እንደሚሉት ነግረውት ነበር፡፡
ጌታችንም እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ ሲላቸው ቅዱስ
ጴጥሮስ እንዲህ አለ፡፡ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ
ነህ፡፡ ጌታችንም የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ
እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን
እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። ብሎታል፡፡ የእግዚአብሔር
ልጅ መባሉ እንደ ሰዎች በመሰለ ልደት አይደለም፡፡ ከፍጥረታት በፊት(ጊዜን ጨምሮ) ያለ እናት የተወለደው የማይመረመር ልደት
ነውና መበላለጥ ፣ መቀዳደም የሌለበት፣ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ያልሆነበት ስለሆነ ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ነው፡፡
ለዚህም ነው በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት፣ ሦስት ስሞች፣ ሦስት ግብራት አንድ እግዚአብሔር
የምንለው፡፡ እግዚአብሔርን አማላጅ ማድረግም እብደት ነው፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ስብሐት
ለማርያም፣ ስብሐት ለመስቀለ እግዚእነ