ያልዘመነ “ዘመናዊነት”
ሉላዊነት- ዐለምን በራሳቸው አስተሳሰብ ለመምራት ከሚደክሙ፣ የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት የሚመነጭ እንቅሰቃሴ ቢሆንም በዋናነት “ምዕራባዊነት” ተብሎ
ሊወሰድ ይችላል። ይህም ጥቂቶች በሚያራምዱት፣ ብዙዎች በሚነጉዱበት በምዕራቡ ዐለም(አውሮፓና አሜሪካ) አስተሳሰብ መመራት ነው።
በሉላዊነት፣ የምዕራቡ ዐለም
ፍላጎት ላይ ላዩ ሌላ
ቢመስልም በዋናነት የጥቂቶችን የበላይነት ለማስፈን ልዩ
ልዩ ስልቶችን በመጠቀም እግዚአብሔር የለሽ
የዐለም ስርዓት እንዲፈጠር መስራት ነው፡፡ (The New World Order. A.Ralph Epperson,2009)። ዘመናዊነትም ትክክለኛ ትርጉምና መገለጫ ሳያገኝ በግርግር ለዚህ
እኩይ ዐላማ ሲውል ይስተዋላል።
“ዘመኑን ምሰል፣ፈታ በዪ፣ላይፍ ነው…”
የሚሉ ያልተጤኑና ያልተብራሩ “የሕይወት መመሪያዎች” የስንቱን ወጣት
የስነ ልቡና የበላይነት ወስደው ኪሳራ
እያደረሱ ይሆን!
ሥራ
የሚሠራበት የወጣትነት ዕድሜ በልዩ
ልዩ ሱሶች በመያዝ፣ በከፍተኛ ድብርት ውስጥ
በመግባት፣ ተቃራኒ ጾታን ለማማለል “ውበትን ፍለጋ”
በመድከም፣ የወሲብ ፊልሞችን በማየት፣…የማያስብ ሰው(እንስሳ) ሆኖ የሚባክን ዕድሜ
እንዲሆን የሚገፋፉ መንገዶች እየበረከቱ መጥተዋል። እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑም የዘመናዊነት መለኪያ፣ ሕይወትን በቀላሉ የመኖር መገለጫ ተደርገው መወሰዳቸውና በሕብረተሰቡ ዘንድ
የቆየው ተግባራቱን የመጸየፍ አመለካከት የተሳሳተና ኋላ
ቀር ተደርጎ እንዲቆጠር በቀጥታም ይሁን
በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽዕኖ ማሳረፋቸው ችግሩን ከባድ
ያደርገዋል።
ዘመናዊነት ምንድነው? የሕይወት መመሪያስ ከየት ይቀዳል?
አሁን
አሁን ዘመናዊነት(የሐሳብ ልዕልና) በሐሳብ ትሕትና(ዝቅተኝነት) የተተካ ይመስላል። ለዘመኑ ሰው
“ለራስ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ
ከተገኘ መደረግ ያለበትን አለማድረግ፣ መደረግ የሌለበትን ማድረግ” ይቻላል። የቤተሰብን ሀብት
በብቸኝነት ለመውረስ ወንድምና እህትን መግደል፣ የአንዲትን ሀገር
ሀብት ለመዝረፍ ያችን ሀገር
ወደ ጦርነት ማስገባት፣ ለጥቂቶች የበላይነት ሲባል
ማሰብ የማይፈልግ፣ ለሱስና ድብርት የተጋለጠ ትውልድ እንዲፈራ ማድረግ፣ ”መብታቸው ነው”
በሚል ፈሊጥ ዝሙትና ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፉ ዕድል
መስጠት…ለ”ዘመኑ ሰው
ዘመናዊነት” ነው።
ራስን
እንዴት መጥቀም ይቻላል? ብዙዎቻችን እንደሚመስለን “ራስን
መጥቀም” ራስን መጥቀም ሳይሆን፤”ራስን
መጥቀም” ራስን መጉዳት፣”ራስንም መጉዳት” ራስን
መጥቀም በመሆኑ “ራስን መጥቀም” በሚል
ምድራዊ ሒሳብ እያሰሉ የሚጓዙት በቅድሚያ ራሳቸውን ይጎዳሉ።”ነፍሱን የሚያገኛት ያጠፋታል፤ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋት ያገኛታል።”/ማቴ.10፣39/
ስለዚህ ዘመናዊነት በዘላቂነት ራስን
መጥቀምን እንጂ ጊዜያዊ ጥቅምን፣ዘመኑ የሆነውን መሆንን ወይም
አለመሆንን ሊያመለክት አይገባም። የሰው ልጅ እውነትን ሲከተልና በእውነት ሲጸና
ራሱን በዘላቂነት ይጠቅማል።
የዐለም ዘመናዊነት ኅልፈት ያለበት(የሚያልፍ) ነው። ስለዚህም ‘የአሁኑ አያድርገውና በዚያ
ዘመን እንዲህ ነበርኩ…’ ይባልበታል። በክርስትና ያለው
ዘመናዊነት ግን ኅልፈት የሌለበት ነው።
እውነተኛ ክርስቲያን ትናንትና፣ ዛሬ፣
ነገም ዘመናዊ ነው።
የክርስቲያን ዘመናዊነቱ ዘልዐለማዊነት(የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዘለዐለም ወርሶ፣በፍቅሩ ሆኖ፣ንጽጽር በሌለው በፍጹም ደስታ
መኖር) ስለሆነ በዘመን ብዛት
ኋላ ቀርነት፣ በዘመን መለወጥም ዘመናዊነት የለበትም።
በክርስትና ወይም
እውነት(እውነት የሆነውን ክርስቶስን ትሰብካለችና) መነጽር ሲታይ ዘመኑ
ሊያዘምነን እየደከመ ያለው ባልዘመነ ዘመናዊነት ነው። ይህም የስም
አሳሳች ሆኖ የቀረበ እንጂ
እውነተኛው ዘመናዊነት አይደለም። ዐለም ፍላጎትዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሳይንስ ያልሆነውን ‘ዝግመተ ለውጥ’ን በሳይንስ ስም
እንደምትግተን ሁሉ በዘመናዊነት ስምም
ያልዘመነ ዘመናዊነትን እየጋተችን እንደሆነ ማስተዋል ይገባል።
ትርፉ
በአግባቡ ካልተሰላ፣ በጊዜ ከተገደበ፣ በየዘመኑ እየተቀያየረ በዘመናዊነት ስም
ከሚመጣው የዐለም ሸክምና ባርነት ይልቅ ሁሌም
አዲስ በመሆኑ በየዘመኑ መታደስ በማያሻው ዘመናዊነት(ክርስትና) ዘመንን ማሳለፍ እጅግ
አትራፊ ነው።
የሰው
ልጅ የሕይወት መመሪያ፣ ደስታው፣ ሐዘኑ፣ ሀብቱ፣ ድህነቱ፣ አኗኗሩ፣ ዓላማው፣ በአጠቃላይ ሁለንተናው መቀዳት ያለበት ከራሱ
ፍላጎት ወይ ሌሎች በራሳቸው ሐሳብ
ለራሳቸው ዓላማ ከቀየሱለት መንገድ ሳይሆን ከእውነት ነው።
የሕይወት መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ
እውነት እግዚአብሔር እንደሆነ እንዲህ በማለት ይነግረናል።”የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ።”/ዮሐ.14፣6/
የጭንቀት ቀን
ሳይመጣ፣ በጉብዝና ወራት ፈጣሪ የሚታሰበው ጥልቅ
ፍቅሩ በእኛ እንዲኖር ዐለም
ከምታቀርብልን ማታለያ በመሸሽ፣ የልባችንን መቅደስ በሃይማኖት በመጠበቅ፣ በምስጢራት በመታተም፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ራስን
ለማሳደግ በመጋደል፣ ስለሌላው መዳን
የድርሻን በመወጣት ዐለምን እምቢ
እግዚአብሔርን እሺ በማለት ነው።
ዕውር
ዕውርን እንዳይመራው፤ ያልዘመነው ዘመናዊነት አስቀድሞ ይዘምን፤ እኛም
ያኔ እንገናኘዋለን። ያልዘመነውን የዐለምን ዘመናዊነት ለማዘመን እውነተኛ ዘመናዊ ሆነን
መገኘት ይኖርብናል። ይህንንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላልዘመነው ዘመናዊነት ተጋላጭ ከሆነው ወጣቱ
ትውልድ አብዝታ ትሻዋለች።
የቅዱሳን ምልጃ፣ የእግዚአብሔር ረድኤት አይለየን።