Sunday, November 17, 2013

ታላላቆች ፊደላት



(ክፍል ፩ )
መምህረ ወንጌል ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ ከላካቸው አሥራ አራት መልእክታት ውስጥ ወደ ገላትያ ሰዎች የላካት የመጀመሪያይቱ እንደሆነች ይታመናል፡፡የዚህች መልእክት ይዘት በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን አካትታ ከያዘቻቸው ጉዳዮች ውስጥ በምዕራፍ ስድስት ስለ በደለ ወንድም፣ ስለ ሥጋና መንፈስ ዘር የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ሀ) ስለ በደለ ወንድም
በሃይማኖት የሚመስለን አብሮን የሚኖር ሰው ወንድማችን ነው።ለክርስቲያናዊ ሕይወቱ ዕንቅፋት የሚሆንበት ክፋት ቢገኝበት የአንድ ክርስቲያን ድርሻ ምንድን ነው?
የክርስትና ዓላማ የሰውን ልጅ ለሰማያዊ ክብር ማብቃት ነው፤ስለዚህም የአንድ ክርስቲያን ድርሻ ከዚህ እውነት የሚቀዳ ይሆናል።ሰው በማናቸውም በደል እንኳ ቢገኝ ማቅናት/ወደ ቀናው መንገድ መምራት በመንፈሳዊ ሕይወት የሚጓዝ ክርስቲያን ተግባር ነው።አንድ ክርስቲያን በክርስቲያን ወንድሙ ላይ በአግባቡ ሊያገባው ይገባል።
የሰውን ጉድፍ ስለምን አያለሁ? ጉድፉ እንዲወገድ ስለምፈልግ ነውን? የወንድሜ ጥፋት ስለምን ይታየኛል? ሕይወቱ የተስተካከለ እንዲሆን ስለምሻ ነውን? ወይስ የእርሱ የበደል ብዛት የእኔ አለመበደል ማረጋገጫ ስለሚሆነኝ? ደግሞስ በደሉን የምነግረው እንዲቃና አስቤ ነውን? ወይስ በደሉን በመንገሬ እየተሳቀቀ፣ እየሸሸ አልያም ከእኔ በታች እንደሆነ አምኖበት እንዲኖር? ወይም “በቃሌ ትምህርት በሥራዬ አርአያነት የለወጥኩት ሰው ይከው “ የሚል የመመኪያ ሃውልት ለማስቆም በመፈለግ? እግዚአብሔር ረድቶን የወንድማችን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሻሻል መሰረታዊ ፍላጎት ቢኖረን እንኳ እኛ ከእርሱ በላይ መሆናችንን ነጥብ በማስቆጠር ሥጋዊ ደስታን የምንሰበስብበት ረቂቅ ስልት የመሆን ዕድል አለው።
ስለዚህ የበደለውን ወንድም ማስተካከል ፍላጎቴ ከሆነ በየውሃት መንፈስ እንዳቃናው ተነገረኝ፤የራስ ሥጋዊ ጥቅምን ለማግኘት የሚል ሌላ ስውር ሆነ ግልጽ ዓላማ የሌለበት ማቃናት እንዲሆን፣ወንድምን ከማሳቀቅ የራቀ እንዲሆን ሊጤን ይገባል።እኔም በደል የማይደርስበት፣ እንዳይደርስበትም በንጽሕናው ዋስትና ያገኘ ሰው አይደለሁምና ወንድሜን ሳቃና በቅንነትና ራስን በማየት መሆኑን መመርመር ይጠበቅብኛል።
ለ) ስለ ሥጋና መንፈስ ዘር
የሥጋ አስተሳሰብን መሰረት አድርገን የምንጓዘው መንገድ ከእግዚአብሔር ለይቶ የኃጢአት ተገዢ ወደ መሆን ያደርሰናል።የሥጋ ዘር ቢዘራ የሥጋ ፍሬ ይለቀምበታል፤የመንፈስ ዘር ቢዘራ የመንፈስ ፍሬ ይለቀምበታል። በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለፀው በሥጋ የሚዘራው የዝሙት፣ የገዳይነት፣ የምቀኝነት ፣የዘፋኝነት፣ የራስ ወዳድነት …ዘር የሞትን ፍሬ ያፈራል፤በመንፈስ የሚዘራው የፍቅር፣ የትዕግስት ፣ የበጎነት፣ ራስን የመግዛት…ዘር የሕይወትን ፍሬ ያፈራል።  ሰው በሰውነቱ የመንፈስን ዘር ዘርቶ የመንፈስን ፍሬ ያጭድ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
በሥጋ ዘር የመንፈስን ፍሬ መልቀም ከቶ እንዴት ይቻላል! ወንድሜ ሆይ የመንፈስን ፍሬ በሥጋ ዘር ታገኛት ዘንድ ምን ያህል ደከምህ! አንተ ትዘፍናለህ ነገር ግን አመስጋኝ ነኝ ትላለህ ፤ አንተ ትቀየማለህ ነገር ግን ይቅር ባይ እንደሆንክ ታስባለህ ፤አንተ ትጣላለህ ነገር ግን ፍቅርን የምታውቃት ይመስለሃል፤ አንተ ታመነዝራለህ ነገር ግን ራስህን የምታውቅ ጠንቃቃ አማኝ፣ አገልጋይ አድርገህ  ትቆጥራለህ።በሥጋ ዘር የመንፈስን ፍሬ ለመልቀም መጣጣር ምንኛ አድካሚና የማይቻል ነው! ቢሆንም አሁንም ይህንኑ እናደርገዋለን ።ይህ ተግባራችን የድንጋይን  ግንብ ለማፍረስ በእጁ እየገፋ የሚውል ምስኪን ሰውን ያስመስለን ይሆን? ግንቡ ፈጽሞ ፈቅ የማይል መሆኑን ቢያውቅም የተሻለ አማራጭ ከመፈለግ ይልቅ አሁንም እንዲሁ ያደርጋል፤ ምናልባትም እንዲህ አድርጎ አልገፋ ሲለው ለምን ብሎ ይበሳጭ ይሆናል።
የኃጢአት ግድግዳን ለመግፋት፣ የዝሙት ጾርን ለማራቅ፣ ከምቀኝነት መንፈስ ለመላቀቅ፣ ከምስጋና የለሽ ሕይወት ለመጠበቅ የመንፈስን ዘር ዝራ።የመንፈስ ዘር ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ፣ከአባቶች ጋር መተዋወቅ ፣ወደ ገዳም መሄድ ፣በመንፈሳዊ ተቋም መማር፣ የሰንበት ት/ቤት ወይ የአገልግሎት ማኅበር አባል ወይ አስተባባሪ መሆን፣ የሰበካ ጉባኤ አባል መሆን ፣ማስቀደስ ፣መቀደስ፣ መስበክ፣ መሰበክ በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ለታቦታት ምንጣፍ ማንጠፍ ብቻ እንዳይመስልህ ይህን ሁሉ በጥልቀት የሚያስብ ጥልቅ መንፈሳዊነትም ጭምር እንጂ ።
ሐዋርያው እነዚህን ሀሳቦች ሲያጠቃልል እንዲህ ይላል፤” እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደጻፍሁላችሁ እዩ”(ገላ.፮፣፲፩)፡፡ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ታላላቆች ፊደላት፤በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በታላላቆች ፊደላት የተመላ ነው፤የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ስርዓት ትውፊት አጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎቷ ምንኛ በታላላቆች ፊደላት የተዋቡ ናቸው!ለማሳያነት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጥቂቶች ታላላቆች ፊደላት እንመለከታለን፡፡
ታላላቆች ፊደላት
ጠላትነትን አደርጋለሁ (መጽሐፍ ቅዱስ)
በአጭሩ ተናገሩ (መጽሐፍ ቅዱስ)
እምነት ጨምርልን (መጽሐፍ ቅዱስ)
ቁርጥ ልመናችንን ስማን (መጽሐፈ ኪዳን)
የተጨነቀችይቱን ነፍስ ሁሉ አሳርፍ (መጽሐፈ ቅዳሴ)
ከተቀራረቡ ተራሮች መሠረት …የኃጢአቱ ክብደት የሚበልጥ …(መጽሐፈ ምስጢር)
የምጽፍባትን ብዕር ስበራት ስበራት አለኝ (አረጋዊ መንፈሳዊ)
እኔ ቸል ስል ሞት ደርሶብኛል(ውዳሴ አምላክ)
ሰጠሁ ተቀበልኩ (ዮሐንስ አፈወርቅ)
ኑ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ (ገድለ ጊዮርጊስ)

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።