Wednesday, October 9, 2013

እምነት ምንድን ነው?(ክፍል ሀ)


           እምነት የተወሰነን ነገር ወይ  ሁሉንም ነገር ኃይል ብለው ለሚቀበሉት ለአንድ አካል ወይ ለብዙ አካላት ባለቤትነት መስጠት ነው።ስለዚህም በማመን ውስጥ የሚያምንና የሚታመን አሉ።ከዓለም ታሪክ እንደምንረዳው ሰዎች ስለ ተወሰነ ጉዳይ ወይ ስለ ሁሉም ጉዳዮች አንድን ወይ ብዙ ነገሮችን  ይከተላሉ።በአጠቃላይ በማመን ውስጥ ለአጭር ጊዜም ይሁን ለዘለዓለም፣ ለውሱን ጉዳይ ይሁን ለሁሉም ጉዳዮች ለአንድ ወይ ለብዙ አካላት ተገዢ መሆንን ያመለክታል፤ማድረግ አለማድረግ መማር መቅጣት … የሚችል/ሉ አካል/ላት እንዳለ/ሉ መቀበልን ያሳያል።
           ሰው ወንዙን፣ ተራራውን፣ ዛፉን፣ ድንጋዩን፣ እሳቱን፣ ጉልበቱን፣ አስተሳሰቡን፣የማይታይን አምላክ… ያምን ይሆናል።”እምነት አለ፤ የለም፤” ብሎ ከመከራከር ይልቅ “እምነት ስንት ነው? እውነተኛና ሐሰተኛ እምነትስ አለ ?” ብሎ መጠየቁ ይበልጥ ሚዛን ይደፋል።ምክንያቱም ሰው “በምንም አላምንም” በማለት ከእምነት ውጭ መኖር እንደሚችል ያሳየ ቢመስለውም “በምንም አላምንም” በሚለው አስተሳሰቡ ያምናል ማለት ነው።”ራሴንም እጠራጠራለሁ” ቢልም እንኳ “ራሱን በመጠራጠሩ” ያምንበታል ማለት ነው።ስለዚህ የሚያምነው ነገር እና ዓላማ ሊለያይ ይችላል እንጂ ምንም የማያምን ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው።በተለምዶ እምነት የሌላቸው (እምነት የለሽ) ሰዎች የሚባሉ ይኖሩ ይሆናል፤ይህ ማለት ከራሳቸው (አስተሳሰባቸው) በቀር የሚያመልኩት ሌላ አካል የሌላቸው መሆኑን ለመጠቆም የተቀመጠ ነው።ስለ ሁሉም ጉዳይ ዘልዓለማዊ የሆነውን የፈጠረውን እንጂ ያልተፈጠረውን አምላክ ማመን ይገባል።
አምልኮ በአንድ አምላክ

            በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች አንድ ሁሉን ቻይ ዘልዓለማዊ እና የማይታይ አምላክ እንዳለ ያምናሉ፤ነገር ግን አንድ እምነት የላቸውም፤ምክንያቱ ምንድነው?
            ምንም እንኳ በአንድ ዘልዓለማዊ  የማይታይና ሁሉን ቻይ አምላክ ማመን አንድነት ቢሆንም ያልተብራራ አንድነት እንደሆነ ደግሞ ግልጽ ነው።ስለዚህ የእምነት አንድነት በአንድ የማይታይና ሁሉን ቻይ ዘልዓለማዊ ፈራጅ ፈጣሪ…ከማመን በላይም የሚፈልገው ሌላ አንድነት አለ።ይህ አምላክ ምን ባህርያት አሉት(አንድነት ሦስትነት፣በተለየ አካል ሰው መሆን…)? የሰጣቸው ትእዛዛት ፣ለሰው ልጅ የሰጠው ተስፋ፣ ያስቀመጠው የድኅነት መንገድ፣ ስለ ዘልዓለማዊ ሕይወት ያለው ትምህርት ምንድን ናቸው?…የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።እነዚህን ጥያቄዎች ፈጽሞ ማለፍ የማይቻል በመሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች የተለያዩ መልሶች ያሏቸው ሁሉ የተለያዩ እምነቶች ሊሆኑ የግድ ነው።ስለዚህም በእምነት ፈጽሞ አንድ አይደሉም።
          ይህም ማለት ከኤስያ ተነስተው ወደ ኢትዮያ ለመምጣት የወሰኑ ሰዎች  አንዱ ወደ ካናዳ ፣ሌላው ወደ ስፔይን ፣ሌላው ደግሞ ወደ ሞሮኮ የመሄድ ያህል ይሆናል።በኢትዮያ ያሉትን ክፍላተ ሀገር ፣ወንዞችና ተራሮች ፣ሰዎች ፣ታሪኮች …(ፍጹም ራሳቸውን ሆነው) በካናዳ ወይ በስፔይን ወይም ደግሞ በሞሮኮ አገር ማግኘት ከቶ እንዴት ይቻላቸዋል? ስለዚህም እነዚህ ሰዎች ኢትዮያን ጎበኘናት፤ እናውቃታለን፤ ብለው ቢናገሩ ስተው ከማሳት በቀር ሌላ ምን ይፈይዳሉ!
         በመሆኑም ሁሉም እምነቶች ሊያድኑ አይችሉም ፤ የሚያድን አንድ ትክክለኛ እምነት ብቻ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።ሰዎችም የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉት “ማዳን ከሚችሉት ከተለያዩ እምነቶች አንዱን ልከተል” በሚል ሳይሆን “ብቸኛ የድኅነት መንገድ የሆነውን እምነት ልከተል” በሚል መሆኑ የታወቀ ነው፤ስለዚህ በየእምነቱ ያለ ሰው የሚያምነው እምነት ብቻ ትክክለኛ  መሆኑን መመስከሩ ሊያስነቅፈው አይችልም።ይህ ማለት ግን ሌላው የፈለገውንና አምንበታለሁ የሚልበትን  እምነት የማመን መብት የለውም ማለት አይደለም።

መስቀል፡ የምንቀብረው ወይስ የምንሸከመው?

   ''ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር እንጂ ከተሰቀለበት መስቀሉ ጋር ምን አለን...'' ለሚሉት ግሩም ምላሽ ይመልከቱ።